አስተዳደራዊ ውሳኔ ሰጭነት (ከፊል የዳኝነት ስልጣን)
-ስልጣንና ተግባራት
የስልጣን ምንጭ
የመንግስት ስልጣን በህግ ከተቀመጠለት ገደብ እንዳያልፍና ይህንንም በተግባር ለማረጋገጥ መጀመሪያ የስልጣንን ምንጭ እና መገለጫ ባህርያት በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለመሆኑ ስልጣን ከየት ይመነጫል? እንዴትስ ይገለጻል? የስራ አስፈፃሚውና የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች የስልጣን ምንጭ ህግና ህገ መንግስት ብቻ ነው፡፡ በህገ መንግስታዊ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው የመንግስት ባለስልጣናት ስልጣን በህዝብ ከተመረጡ ተወካዮች የመነጨ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ስልጣናት ጠቅለል ባለ አነጋገር ይዘረዝራል፡፡ የእያንዳንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስልጣንና ተግባር ብዙውን ጊዜ አዲስ የምርጫ ዘመንን ተከትሎ በተወካዮች ምክር ቤት የሚወጣው የስራ አስፈፃሚውን ስልጣንና ተግባር የሚወስን አዋጅ ላይ ተዘርዝሮ ይቀመጣል፡፡የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት በይፋ ከታወጀ ወዲህ የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጡ አዋጆች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ይህ መጽሐፍ ወደ ህትመት እስከገባበት ጊዜ ድረስ ፀንተው ያሉ ህጎች አዋጅ ቁ. 916/2008 እና አዋጅ ቁ. 942/2008 (ማሻሻያ) ሲሆኑ የተቀሩት በሙሉ ተሽረዋል፡፡የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጡ አዋጆች ዝርዝር፤
አዋጅ ቁ. 4/1987
አዋጅ ቁ. 93/1990 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 134/1991 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 256/1994
አዋጅ ቁ. 380/1996 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 411/1996 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 465/1997 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 471/1998
አዋጅ ቁ. 546/1999 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 603/2001 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 641/2001 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 642/2001 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 691/2003
አዋጅ ቁ. 723/2004 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 803/2005 (ማሻሻያ)
አዋጅ ቁ. 916/2008
አዋጅ ቁ. 942/2008 (ማሻሻያ)
የሌሎች የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ስልጣን ደግሞ የተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው አዋጅ እንዲሁም ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብa በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ ተደንግጐ ይገኛል፡፡ እነዚህ በየጊዜው የሚወጡ ማቋቋሚያና ሌሎች ተጓዳኝ ህጐች የአስተዳደሩ የስልጣን ምንጭ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ስለሆነም የአስተዳደር መ/ቤቶችን የስልጣን ገደብ ለመወሰን የተወካዮች ም/ቤት ያወጣውን አዋጅ ብቻ ሳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቦችን ማመሳከር ያስፈልጋል፡፡ ከሁለቱ ህጎች ውጭ ከልማድ፣ ከመመሪያ ወይም ከሌላ የስልጣን ምንጭ በማንኛውም የአስተዳደር መ/ቤት የተፈጸመ ድርጊት፣ የተሰጠ ውሳኔ፣ የወጣ መመሪያ ወይም ደንብ ከስልጣን በላይ እንደ መሆኑ ህጋዊነት ኖሮት በህግ ፊት ሊፀና ሆነ ውጤት ሊኖረው አይችልም፡፡ በህግና በህጉ መሰረት መሰረት ብቻ መስራት የህግ የበላይነት የቆመበት ምሶሶ እንደመሆኑ የህዝብ ወይም የመንግስት አስተዳደር ሊከናወን የሚገባው ከህግ በመነጨ ስልጣን መሰረት ብቻ ነው፡፡
4-አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን
የቋንቋ ጉዳይ
በአንዳንድ ህጎች የሚገኙ ቅድመ ሁኔታዎች
4-አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣንባህርያትና የስልጣን ምንጭ
አስተዳደራዊ ድንጋጌ ማለት ከህግ አውጭው በተሰጠ የውክልና ስልጣን ገደብ ውስጥ በስራ አስፈፃሚውና የአስተዳደር መ/ቤቶች የሚወጣ የበታች ህግ (subordinate legislation) ነው፡፡ በውክልና ህግ ማውጣት የአስተዳደር ህግ አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ የስራ አስፈፃሚው አካል ህግ የማውጣት ስልጣን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት የነፃ ገበያ ክስተትን ተከትሎ የመጣው ዘመናው የማህበራዊ ደህንነት መንግስት (welfare state) ካስመዘገባቸው እድገቶች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡በውክልና ህግ ለማውጣት ዋናው የስልጣን ምንጭ ህግ አውጭው እንደመሆኑ የተወካዮች ም/ቤት በማያወላውልና ግልጽ በሆነ መልኩ ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ወይም ለአስተዳደር መ/ቤቶች ካልሰጠ እነዚህ አካላት ከህገ መንግስት የመነጨ የህግ አውጭነት ስልጣን የላቸውም፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት የሚኒስትሮች ም/ቤት ሆነ የአስተዳደር መ/ቤቶች ደንብና መመሪያ እንዲያወጡ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ስልጣን አይሰጣቸውም፡፡ በፌደራል ደረጃ ህግ የማውጣት ስልጣን የተወካዮች ም/ቤት ሲሆን በክልል ደረጃ ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ህግ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው አካል በህገ-መንግስቱ ላይ የለም፡፡የውክልና ስልጣን በሌለበት ሁኔታ የሚወጣ ማንኛውም ደንብ ሆነ መመሪያ ከስልጣን በላይ እንደመሆኑ የህጋዊነት መስፈርትን አያሟላም፡፡ በእርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማው ፀድቆ ከታወጀ የሚኒስትሮች ም/ቤት ውስን ለሆነ ጊዜ ሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶችን ደንብ በማውጣት ሊገድብ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ የሚኒስትሮች ም/ቤት በቀጥታ ደንብ ለማውጣት የሚችልበት ህገ መንግስታዊ ስልጣን የለውም፡፡የስልጣኑ ምንጩ የተወካዮች ም/ቤት ብቻ ነው ከተባለ ይህ አካል ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ በውክልና ማስተላለፍ ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመርመሩ ተገቢ ሆናል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ላይ ይህን የሚፈቅድለት ግልጽ ድንጋጌ የለም፡፡ ብዙዎች የመስኩ ምሁራን እንደሚስማሙበት ግን ህግ አውጭው ስልጣኑን በከፊል በውክልና ለማስተላለፍ ከህግ አውጭነቱ የሚመነጭ ስልጣን (inherent power) አለው፡፡ እንዲያም ሆኖ ያለገደብ ከህዝብ የተሰጠውን ስልጣን በውክልና ስም ሊያስተላልፍ አይችልም፡፡በመሰረቱ በውክልና ስልጣን የሚወጣ ህግ ከመንግስት አስተዳደር እየተለጠጠ መምጣት ጋር ተያያዥ የሆኑ አስገዳጅ ሁኔታዎች ያመጡት ክስተት ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ልዩ ሁኔታ እንጂ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት የለውም፡፡ ህግ አውጭው ምንም እንኳን በከፊል ስልጣኑን ማስተላለፍ ቢኖርበትም የፖሊሲ ጥያቄዎችን የሚነኩ መሰረታዊ ጉዳዮች በደንብ ወይም በመመሪያ እንዲወሰኑ ውክልና መስጠት የለበትም፡፡ የተፈጻሚነቱ ወሰኑ በህግ አውጪው በሚወጣው ህግ ላይ የሚታዩ ቀዳዳዎችን ለመድፈን ብሎም የፖሊሲ ጥያቄዎችን በማይነኩ ዝርዝርና ጥቃቅን ቴክኒካል ጉዳዮች መገደብ አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር አፈጻጸሙ በጠባቡ ሊሆን ይገባዋል፡፡አስፈላጊነትብቁና ውጤታማ አስተዳደር እንዲሰፍን የአስተዳደር መ/ቤቶች በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን፣ ተግባርና ግዴታ በተጨባጭ ማሳካት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስኬት እንዲኖር ደግሞ የማስፈፀም ስልጣን ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ ጠቅለል ያለ ይዘት ያላቸው በፓርላማ የሚወጡ ህጐች የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ከመጠቆም ባለፈ ቴክኒካልና ዝርዝር ጉዳዮችን ስለማይዳስሱ በየጊዜው ለሚነሱ ችግሮች ወቅታዊና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ይሳናቸዋል፡፡ ስለሆነም አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን አስፈላጊነት ከሁለት አቅጣጫዎች ማለትም ከአስተዳደር ስራ ውጤታማነት እና ከህግ አውጭው ውስንነት አንፃር ሊቃኝ ይችላል፡፡
አስፈላጊነቱ ጎልቶ ቢታይም በመስኩ ሊቃውንት ጠንካራ ተቃውሞ ሳይገጥመው አልቀረም፡፡ እንደ ብዙዎች እምነት የአስተዳደር መ/ቤቶች ህግ የማውጣት ስልጣን በዜጐች መብት ላይ በሩን ዘግቶ ወደ አምባገነናዊነት የሚያመራ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ተቃውሞው መሰረቱ ንድፈ ሀሳባዊ ሲሆን የስልጣን ኢ-ተወካይነት ንድፈ ሀሳብ (theory of non delegability of power) አንዱ ነው፡፡ በላቲን potestas delegari non potest delegare ተብሎ ሲጠራ በእንግሲዝኛው power once delegated should not be re-delegated የሚል ይዘት አለው፡፡ ይህም ወደ አማርኛ ሲመለስ ‘በውክልና የተሰጠ ስልጣን እንደገና በውክልና ሊተላለፍ አይችልም’ እንደ ማለት ነው፡፡ በአጭር አገላለፅ ህግ አውጭው ህግ የማውጣት ስልጣኑን የሚያገኘው ከመራጩ ህዝብ እንደመሆኑ ይህን በአደራ የተቀበለውን ስልጣን እንደገና (በድጋሚ) በውክልና ማስተላለፍ የለበትም ማለት ነው፡፡aየህግ አውጭነት የስልጣን ምንጩ ህዝብ ነው፡፡ የአንድ አገር ህዝብ ተወካዮቹን ሲመርጥ ችሎታና ብቃታቸውን መሰረት አድርጐ ‘ያስተዳድሩኛል፤ ለእኔ ይሰሩልኛል፣ ትክክለኛውን ህግ ያወጡልኛል’ በሚል እምነት ጥሎባቸው ነው፡፡ ህግ አውጭው በውክልና በአደራ ከህዝቡ የተቀበለውን ስልጣን በአግባቡ በመገልገል ልማት፤ እድገት፤ ፍትህ፣ መልካም ስርዓትና ሰላም የሚያሰፍኑ ህጐችን ማውጣት አለበት፡፡ ህዝቡ ድምፁን ሰጥቶ ተወካዮቹን ሲመርጥና ስልጣን ሲሰጥ ይህን የህግ አውጭነት ስልጣን ላልተመረጡ ግን ለተሾሙ ስራ አስፈፃሚዎች በውክልና እንዲያስተላልፉት አይደለም፡፡ ከዚህ ሀሳብ በተቃራኒ ስልጣን በውክልና ከተላለፈ ህዝቡ ድምፅ ሰጥቶ ባልመረጣቸው ስራ አስፈፃሚዎች እየተገዛ ነው፡፡ሁለተኛው የውክልና ህግ ንድፈ ሀሳባዊ ተቃውሞ ከስልጣን ክፍፍል መርህ (separation of powers) የሚነሳ ሲሆን ዞሮ ዞሮ መሰረቱ የአስተዳደር በደል እንዲንሰራፋ ያደርጋል የሚል ነው፡፡ በስልጣን ክፍፍል መርህ መሰረት ህግ ማውጣት ለህግ አውጭው፤ ህግ መተርጐም ለፍርድ ሰጭው፤ ህግ ማስፈፀም ለአስፈፃሚ ተብሎ የእያንዳንዱ የመንግስት አካል ስልጣኑ ተመድቦና ተለይቶ ተሰጥቷል፡፡ አንድ የመንግስት አካል በተደራራቢነት ከአንድ በላይ ስልጣን የያዘ እንደሆነ ከራሱ በላይ ተቆጣጣሪ የሌለው ስልጣኑን እንዳሻው የሚጠቀም አምባገነን ይሆናል፡፡ ስለሆነም ስራ አስፈፃሚው ከተመደበለት ህግ የማስፈፀም ተግባር በተጨማሪ በደንብና መመሪያ ስም ህግ የሚያወጣ ከሆነ ሁለት የመንግስት ስልጣናትን ደርቦ ስለመያዙ ያም የስልጣን ክፍፍል መርህን መጣሱ ግልጽነቱ ጐልቶ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ንድፈ ሀሳብ ተቃውሞዎች መሰረት በውክልና የሚወጣ ህግ አስተዳደራዊ አምባገነናዊነት፤ የአስተዳደር ብልሹነት እና በስልጣን አለአግባብ መገልገል እንዲሰራፋ ያደርጋል በሚል ከመስኩ ባለሙያዎች የሰላ ሂስና ትችት ሲገጥመው ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ እንግሊዝ አገር ውስጥ ሎርድ ሄዋርት የተባሉ የተከበሩ ዳኛና ምሁር በአገራቸው በየጊዜው በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን ‘The New Despotism’ በሚለው መጽሐፋቸው እ.ኤ.አ. በ1931 ዓ.ም. ያቀረቡት ጠንካራ ተቃውሞ የእንግሊዝ ፓርላማ ስለጉዳዩ የሚያጠና አጣሪ እንዲሾምና ምርመራ እንዲያደርግ ምክንያት ሆኗል፡፡b ይሁን እንጂ ከምርመራው በኋላ የቀረበው የምርመራ ሪፖርት (Committee on Ministers’ Powers Report) የደረሰበት ድምዳሜ የውክልና ህግ እንግሊዝ ውስጥ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ይህም በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ተቀባይነት እንደሌለው ካተተ በኋላ በተግባር ግን የግድ አስፈላጊና መቅረት የሌለበት አሰራር መሆኑን በአጽንኦት ገልጿል፡፡cከላይ የቀረቡት ንድፍ ንድፈ ሀሳባዊ ተቃውሞዎች አሳማኝ የመሆናቸውን ያህል እየተወሳሰበ ከመጣው የመንግስት አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተግባራዊ ምክንያቶች አስፈላጊነቱን አይቀሬና የበለጠ አሳማኝ አድርገውታል፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች በህግ አውጭው በሚወጡት አዋጆች ላይ ብቻ ተንተርሰው ውጤታማ አስተዳደር ማስፈን አይቻላቸውም፡፡ በተለያዩ አገራት እንደታየው ህግ አውጭው ከሚያወጣቸው ህጐች በበለጠ የአስተዳደር መ/ቤቶች የሚያወጧቸው መመሪያዎች በፍጥነት እየበዙ መጥተዋል፡፡d በየጊዜው እያደገና እየተወሳሰበ የመጣው የመንግስት አስተዳደር ስራና የህግ አውጭው ለዚህ ስራ ውጤታማነት የሚያግዙ ህጐችን በአይነትና በጥራት ለማቅረብ አለመቻል በውክልና ስልጣን የሚወጣ ህግ አማራጭ ሳይሆን የግድ መሆኑን ያሳየናል፡፡ለዚህም ይመስላል ታዋቂው የአስተዳደር ህግ ምሁር ደብሊው ኤች. አር. ዌድ በውክልና የሚወጣ ህግን “መጥፎ ግን አስፈላጊ” (necessary evil) ሲል የሚገልፀው፡፡e ከህግ አውጭው በሚሰጥ ውክልና ህግ የማውጣት ስልጣንን በተግባር አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡የጊዜ እጥረትህግ አውጭው ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ በውክልና ለማስተላፍ ከሚገደ`ድባቸው ምክንያቶች አንዱ ከራሱ ከህግ አውጭነቱ የሚመነጭ ችግር ነው፡፡ አንድን አዋጅ ለመደንገግ ከሚወስደው ረጅም ጊዜና ተፈጻሚ ከሚሆነው የጠበቀ የስነ-ስርዓት አካሄድ አንጻር ውስብስብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ህጐችን በብዛትና በጥራት ለማውጣት አስቸጋሪ ነው፡፡f የተወካዮች ም/ቤትን ያየን እንደሆነ ከሁለት ወራት የክረምት የእረፍት ጊዜ በኋላ በመካከል ለአንድ ወር ለእረፍት ሲበተን ጠቅላላ የስራ ጊዜው ከዘጠኝ ወራት አይበልጥም፡፡g ከዘጠኙ ወራት ውስጥ ቅዳሜና እሁድ ተቀንሰው በሚቀሩት የስራ ቀናት ባሉት አጭር የስራ ሰዓታት ለአገሪቱ አስፈላጊ አዋጆችን ማውጣት አዳጋች ነው፡፡ የመስኩ ምሁራን እንደሚስማሙበት የአንድ አገር ፓርላማ ለተከታታይ 365 ቀናት ድፍን 24 ሰዓታት በስራ ላይ ቢቆይ እንኳን በብዛትና በጥራት ለአገሪቱ አስፈላጊ የሆኑ ህጐችን ማቅረብ ይሳነዋል፡፡hበተወሰኑ ዘርፎች የተወካዮች ምክር ቤት ያወጣቸው አዋጆች እና በውክልና የወጡ መመሪያዎች ቁጥር ብናነጻጽር ከጊዜ እጥረት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በተግባራዊ ምልከታ ለመመዘን ያስችለናል፡፡ ምክር ቤቱ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ቀረጥና ታክስ በሚመለከት (ማሻሻያዎችን ጨምሮ) ያወጣቸው አዋጆች በቁጥር ከ25 አይበልጡም፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ እነዚህን ህጎች ለማስፈጸም በተለያየ ቅርጽና ስያሜ ተዋቅረው በነበሩትና በኋላም ከሐምሌ 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ስልጣናቸውን አዋህዶ በተረከበው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንi በውክልና ስልጣኑ 129j መመሪያዎች ወጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲሁ የባንክ፣ የመድን፣ የአነስተኛ ፋይናንስ እና የካፒታል ዕቃ ኪራይ ስራዎችን ለመቆጣጠር ከወጡ ወደ ሰባት የሚጠጉ አዋጆችና በሌሎች ልዩ ህጎች በተሰጠው ስልጣን ከ110 በላይ መመሪያዎችን አውጥቷል፡፡k ሌሎች የአስተዳደር መ/ቤቶች እያንዳንዳቸው በቁጥር ወደ 100 የሚጠጉ መመሪያዎች ባይኖራቸውም ከብዛታቸው አንጻር ጠቅላላ ድምሩ ከ1000 ያልፋል፡፡ በዚህ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እስከ ጥር 2008 ዓ.ም. ድረስ ያወጣቸውን 371 ደንቦች ስንጨምርበት በውክልና ስልጣን የሚወጡ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ቁጥር ወደ ላይ በጣም ያሻቅባል፡፡የተወካዮች ምክር ቤት እስከ ነሀሴ 2008 ዓ.ም. ድረስ ካወጣቸው አዋጆች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአጭር ጊዜ የሚወጡ ዓለም ዓቀፍና የሁለትዮሽ ስምምነቶችና የብድር ማፅደቂያ አዋጆች ናቸው፡፡ ስለሆነም ም/ቤቱ ሁሉንም ደንቦችና መመሪያዎች ራሱ ለመደንገግ ቢወስን በተግባር ሊወጣው አይችልም፡፡የእውቀት እጥረትየህዝብ ተመራጮች ለመመረጣቸው ምክንያት እውቀት ወይም ብቃት አንዱ መለኪያ ቢሆንም ዋናው መስፈርት ግን በህዝብ ዘንድ ያላቸው አመኔታና ተቀባይነት ነው፡፡ በጠቅላላ ጉዳዮች ጠቅላላ እውቀት ይኖራቸዋል ብለን ብንገምት እንኳን ከመንግስት አስተዳደር ውስብስብነት አንፃር ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ የበለጠ እውቀትና ችሎታ ያለው በአስተዳደር መ/ቤቶች ዘንድ ነው፡፡l ስለሆነም ፓርላማው ትኩረቱን በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በማነጣጠር ዝርዝር የአፈፃፀም ስልት የሚጠይቁ ቴክኒካል ጉዳዮች በደንብና በመመሪያ እንዲወሰኑ ስልጣኑን በውክልና ማስተላለፍ የግድ ይለዋል፡፡m የእውቀት እጥረት መኖሩ ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር መ/ቤቶች በተቋቋሙለት ዓላማ ስር ልዩና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራታቸው ስልጣንን በውክልና ማስተላለፍ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ተመራጭም ያደርገዋል፡፡ተለዋዋጭ ሁኔታአንድ ህግ ፀድቆ ከወጣ በኃላ ወደፊት ለሚያጋጥሙ ችግሮች በሙሉ በቂ ምላሽ አይሰጥም፡፡ መሰረታዊው ችግር እልባት ቢያገኝ እንኳን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈጠሩ የአፈጻጸም ችግሮች ይኖራሉ፡፡ የህግ አውጭው የህግ አወጣጥ ስነ-ስርዓት የጠበቀና ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑ አንጻር በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን ከተለዋዋጭ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች አንጻር በተከታታይ አዋጅ በማውጣት ምላሽ መስጠት አይታሰብም፡፡ በተቃራኒው አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስነ-ስርዓት እጅጉን የቀለለ እንደመሆኑ ችግሮችን እየተከታተሉ አግባብነት ያለው መፍትሔ ለመቀየስ ያስችላል፡፡n በሌላ አነጋገር ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች ተለዋዋጭ መፍትሔ ለመስጠት አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ፣ ነዋሪ ያልሆኑና ለጉብኝት የመጡ ሰዎች ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው የውጭ ምንዛሪ የሚይዝበትንና ወይም በውጭ ምንዛሪ ክፍያ የሚፈጽምበትን ወይም የክፍያ ማዘዣዎችን የሚይዝበትንና የሚጠቀምበትን ሁኔታዎችና ገደቦች በመመሪያ እንዲወስን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡o እነዚህ ሁኔታዎችና ገደቦች በጊዜ ሂደት የሚለዋወጡ እንደመሆናቸው የተወካዮች ምክር ቤት በቅርበት እየተከታተለ በየጊዜው አዋጅ በማውጣት ቁጥጥር ለማድረግ የህግ አወጣጥ ስርዓቱ አይፈቅድለትም፡፡አስቸኳይ ሁኔታአስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ሲያጋጥም አዋጅ ለማውጣት ከሚያስፈልገው ረጅም ጊዜ አንጻር ፈጣን ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ በተቃራኒው ደንብና መመሪያ በአንድ ሳምንት ምናልባትም ከዚያም ባነሰ ጊዜ ሊወጣ ይችላል፡፡ ስለሆነም ልዩና አስቸኳይ እርምጃ ለመውሰድ አስፈላጊ በሆነበት ሁኔታ ከፓርላማው ይልቅ ስራ አስፈፃሚው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን ሊኖረው ይገባል፡፡ከአስቸኳይነት ጋር ተያያዞ ምስጢራዊነት ሌላው ውክልናን አስፈላጊ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንደኛው ነው፡፡ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝነቱ ባያጠያይቅም ከፊል በሆኑ ሁኔታዎች በአስቸኳይ ሊወሰዱ የታሰቡ እርምጃዎች ደንብና መመሪያው ከመፅናቱ በፊት ቀድመው ከታወቁ ሊሳካ የታሰበው ግብ ይሰናከላል፡፡ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ በሚያስተዳድራቸው ቤቶች ላይ የተፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራት ስርዓት ለማስያዝ በሚል በመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ የወጣው መመሪያ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ መመሪያው በሽንሸና ቤቱን ከተከራየው ግለሰብ የተከራዩ ሰዎች በራሳቸው ስም ከኤጀንሲው ጋር ውል እንዲገቡ ይፈቅዳል፡፡ ኤጀንሲው ሊወስደው ያሰበው እርምጃ ቀድሞ ቢታወቅ መመሪያው ሊያሳካ ያሰበው ግብ ይከሽፋል፡፡ህገ መንግስታዊ ገደብበውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን የአስፈላጊነቱ አጥጋቢ ምክንያት ተግባራዊ ችግሮች ቢሆኑም የመንግስት አስተዳደርን ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ ረገድ ራሱን የቻለ የጐላ ጥቅም አለው፡፡ በእርግጥ የስልጣን አምባገነንነትን ሊያስከትል ከመቻሉ የተነሳ የራሱ አደጋዎችም አሉት፡፡ አደጋውና አላስፈላጊ ጐኑ ሊወገድ የሚችለው ልኩ ተለይቶ በታወቀ ገደብ ውሰጥ ተግባር ላይ የዋለ እንደሆነ ነው፡፡ ውክልናው ግልጽ፣ የማያሻማ፣ ጠባብና ገደብ የተሰመረለት ሊሆን ይገባዋል፡፡የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ህግ የማውጣት ስልጣን ለተወካዮች ም/ቤት እንደተሰጠ በግልፅ ይደነግጋል፡፡a ይህ ስልጣን በውክልና እንዲተላለፍ የሚፈቅድ ግልጽ ድንጋጌ ግን አልሰፈረም፡፡ ስልጣኑን በውክልና እንዲያስተላልፍ የሚፈቅድለት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ባይኖርም የተለያዩ ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ ውክልና ቢያንስ በተዘዋዋሪ የተከለከለ እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል፡፡ በተለይ አግባብነት ያለው የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 77 ንዑስ አንቀጽ 13 የሚኒስትሮች ም/ቤት የተወካዮች ም/ቤት በሚሰጠው ስልጣን መሰረት ደንብ የማውጣት ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንጻር የተጠቀሰው ድንጋጌ ህግ የማውጣት ስልጣንን በውክልና ማስተላለፍ ኢ- ህገ መንግስታዊ ስላለመሆኑ በቂ መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡ለአስተዳደር ህግ አስጨናቂው ጥያቄ ህገ መንግስቱ የተወካዮች ም/ቤት በውክልና ስልጣኑን እንዲያስተላልፍ የመፍቀዱ ነገር ሳይሆን በውክልና ሊተላለፍ የሚችለው ስልጣን ወሰንና ገደቡ የትላይ ነው? የሚለው ነው፡፡ ህግ አውጭው በህዝብ የተመረጠው ህግ ለማውጣት ነው፡፡ ስለሆነም የህግ አውጭነት ስልጣኑን ያለገደብ ወይም ሙሉ በሙሉ ለአስፈፃሚው አካል ማስተላለፍ የለበትም፡፡4በውክልና የማይተላለፉ ጉዳዮችበውክልና የማይተላለፉ ጉዳዮችን በተመለከተ ህገ መንግስቱ የመለሰው ጥያቄ አይደለም፡፡ በመርህ ደረጃ መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን በውክልና ስም ሊተላለፍ አይችልም፡፡ ሰብዓዊና ህገ መንግስታዊ መብትን በቀጥታ የሚነኩ ጉዳዮች፣ የፖሊሲ ጥያቄዎች እና ግብር መጣልን የመሳሰሉ ተግባራት በመመሪያ ሆነ በደንብ ሊወሰኑ አይገባም፡፡ የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ በመመሪያ እንዲያወጣ፣ እንዲያሻሽል ወይም እንዲሽር ስልጣን የሚሰጥ ህግ ኢ-ህጉ መንግስታዊነቱ ፈጦ ይታያል፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ለፖርላማ ቀርቦ በህዝብ በተመረጠ አካል ውሳኔ ሊያገኝበት ይገባልና፡፡ ከመላምታዊ ምሳሌው ባሻገር ይህን መሰል ጥያቄዎች በተግባር ሲመጡ የውክልናውን የስልጣን ገደብን ማስቀመጡ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ ይህን አስመልክቶ የተቀመጠ ህገ- መንግስታዊ ድንጋጌ አለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡የውክልና ወሰንና ገደቡ የት ላይ ነው? የሚለው ጥያቄ ለአስተዳደር ህግ አንገብጋቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ ነውና፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር በመሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣንና በዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮች መካከል ያለው መለያ መስመር የውክልናውን ገደብ ይወስናል፡፡a በእንግሊዝ ፓርላማው ሉዓላዊ እንደመሆኑ በህገ መንግስታዊ ገደብ አይታሰርም፡፡ ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት በዳበሩ ልምዶች በውክልና ሊተላለፉ የማይችሉ ጉዳዮች እየተለዩ መጥተዋል፡፡ በህንድም እንደዚሁ ህገ መንግስቱ በግልፅ ውክልናን ባይፈቅድም ኢ-ህገ መንግስታዊ እንዳልሆነ በህንድ ፍ/ቤቶች አቋም ተይዞበታል፡፡ ሆኖም የገደቡ ልክ ወጥ መስፈርት አልተገኘለትም፡፡ህገ መንግስታዊ ወሰንን አስመልክቶ በሌሎች አገራት ፍ/ቤቶች በተለይም በህንድ ፍ/ቤቶች ከተሰጡ ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው መሰረታዊ ህግ የማውጣት ተግባር በውክልና ሊተላለፍ አይችልም፡፡b መሰረታዊ የህግ ማውጣት ተግባር ማለት የአዋጁን ዓላማ ወይም ፖሊሲ ለይቶ ማስቀመጥና አስገዳጅነት ባለው ህግ መደንገግ ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ህግ አውጭው ደንብና መመሪያውን ለሚያወጣው አካል በቂ ማብራሪያ ሊሆን የሚችል የህግ ማውጣት ፖሊሲ ወይም የአዋጁን ዓላማ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ የህጉ ፖሊሲ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከአዋጁ መግቢያ (preamble)፣ ርዕስ፣ ግብ ወይም ምክንያት ሊገኝ ይችላል፡፡ በተጨማሪም በውክልና የተሰጠው ስልጣን በአግባቡ ለተፈለገበት ዓላማ ስለመዋሉና አውጭው አካል ከስልጣኑ አልፎ ስላለመሄዱ የሚረጋገጠበት በቂ የመቆጣጠሪያ ስርዓት በቅድሚያ መዘርጋት ይኖርበታል፡፡በውክልና ሊተላለፉ አይገባም ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ቀረጥና ግብር የመጣል ስልጣን ነው፡፡c በአገራችን ይህ ስልጣን በፌደራልና በክልል መንግስታት መካከል የተከፋፈለ ሲሆን በፌደራል ደረጃ ቀረጥና ግብር የመጣል ስልጣን የተሰጠው ለተወካዮች ም/ቤት ነው፡፡dከዚህ ውጭ በሚኒስትሮች ም/ቤት ሆነ በየትኛውም የአስተዳደር መ/ቤት የሚጣል ቀረጥና ግብር ህገ መንግስታዊ የንብረት መብትን ይጥሳል፡፡ በእንግሊዝe እና በህንድf ቀረጥና ግብር የመጣል ስልጣን መሰረታዊ ከሚባሉት የህግ ማውጣት ተግባራት መካከል የሚፈረጅ ሲሆን ጥብቅ ከለላም ይደረግለታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሰብዓዊ መብቶችን በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካ ጉዳይም እንዲሁ በደንብ ወይም በመመሪያ ሊወሰን አይችልም፡፡በህግ አውጪው የወጣን ህግ ሙሉ በሙሉ መሰረዝ፣ ማሻሻል፣ የተፈፃሚነቱን ሽፋን ማጥበብ ወይም ማስፋት ሌላው የልቅ ውክልና ምሳሌ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ በእንግሊዝ ስራ አስፈፃሚው ነባር ህግ እንዲያሻሽል ወይም ተፈጻሚነቱን እንዲያስቀር ስልጣን የሚሰጥ የህግ አንቀጽ ‘የሄነር ስምንተኛ አንቀጽ’ (Henry viii clause)g (ወደ አማርኛ አጠጋግተን ስንመልሰው ደግሞ ‘የእንዳሻው አንቀፅ’) ይባላል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ንጉሱ በፓርላማ የወጡ ህጐችን የመሻር ስልጣን ስለነበረው ነው፡፡በተግባር እንደሚታየው ግን በህግ አውጭው የወጣን ህግ በከፊል የተፈፃሚነቱን ወሰን የማጥበብና የማስፋት ስልጣን አልፎ አልፎ በውክልና ይተላለፋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ የተወካዮች ም/ቤት ራሱ ያወጣውን አዋጅ በደንብ ወይም በመመሪያ በከፊል ወይም በሙሉ እንዲሻሻል ሆነ እንዲሰረዝ ስልጣን የሰጠበት አጋጣሚ ባይኖርም የተፈጻሚነት ወሰኑን ማጥበብና ማስፋት በተመለከተ ግን አልፎ አልፎ በደንብ እንዲወሰን ውክልና ይሰጣል፡፡የአስተዳደር መ/ቤቶችን የማቋቋም ስልጣንከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህግ አውጭነት ስልጣን በህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት ገደቦች አልተገታም፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትም የህግ አውጭነት ስልጣኑን ለማስጠበቅ አቅም ያጣ ይመስላል፡፡ በውክልና ሰበብ የሚወጡትን ደንቦች ሊቆጣጠር ቀርቶ መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣኑን ጭምር እያጋራው ይገኛል፡፡ በ2001 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁ. 603/2001a የተወካዮች ምክር ቤት የውክልና ዲሞክራሲን መርህ ከስሩ የሚንድ መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን ለሚኒስትሮች ም/ቤት አስተላልፏል፡፡ ይኸው አዋጅ በአዋጅ ቁ. 691/2001 ቀጥሎም በአዋጅ ቁ. 916/2008 ተተክቷል፡፡ በእነዚህ ህጎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት መነሻና መድረሻ የሌለው የህግ አውጭነት ስልጣን ተጎናጽፏል፡፡ በሶስቱም ህጎች የሚገኘው ድንጋጌ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት፣ ማንኛውም አስፈፃሚ አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈፃሚ አካል ጋር እንዲዋሃድ ወይም እንዲከፋፈል በማድረግ፣ ተጠሪነቱ ወይም ሥልጣንና ተግባሩ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈፃሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን እንዲኖረው ፈቅደዋል፡፡እንዲህ ዓይነቱን ግዙፍ ስልጣን በ1923 ዓ.ም. ህገ መንግስት አንቀጽ 11 እና 34 እንዲሁም በ1948 ዓ.ም. ህገ መንግስት (አንቀጽ 27) ንጉሱ አላስነካም ብለው በብቸኝነት ይዘውት ነበር፡፡ በ1980 ዓ.ም. በቆመው የደርግ ህገ መንግሰት እንዲሁ መ/ቤቶችን የማቋቋም ስልጣን በተዘዋዋሪ ከስራ አስፈፃሚው እጅ አልወጣም፡፡ በአንቀጽ 82/3/፣ 83/1/ እና 86/4/ በተሰጣቸው ስልጣን ዋናዎቹ ህግ አውጭዎች ምክር ቤቱ (Council of State) እና ፕሬዚዳንቱ ነበሩ፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት ግን የስራ አስፈፃሚውን ስልጣን የአስተዳደር ተቋማትን አደረጃጀት ከመወሰን እንዳያልፍ ገድቦታል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 77/2/ እንደሰፈረው የሚኒስትሮች ም/ቤት የሚኒስቴሮችንና በቀጥታ ለራሱ ተጠሪ የሆኑ የመንግስት አካላት አደረጃጀት (በእንግሊዝኛው ቅጂ organizational structure) ይወስናል፡፡ አደረጃጀት ሲባል የአንድን ተቋም ውስጣዊ መዋቅር ይመለከታል፡፡ ማቋቋም፣ ማጠፍ፣ ማዋሃድ፣ መከፋፈል እንዲሁም ስልጣንና ተግባር መለወጥ በህዝብ ከተመረጡ ተወካዮች እጅ መውጣት የሌለበት መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን ነው፡፡በውክልና ዲሞክራሲ መርህ መሰረት የሁሉም ስልጣን መነሻ እና ባለቤት የሆነው ህዝብ የሚያስተዳድሩትን ተወካዮች ሲመርጥ በምርጫው (ወዶና ፈቅዶ) በውክልና ስልጣኑን ያስረክባቸዋል፡፡ በህዝብ ያልተመረጡ የመንግስት ባለስልጣናት እና ሹመኞች ከእነዚህ የህዝብ ተወካዮች በከፊል ተቆርሶ ከሚሰጣቸው ስልጣን በስተቀር ከሌላ ምንጭ የሚያገኙት ስልጣን የለም፡፡ ሆኖም የተሻሩትን ጨምሮ አዋጅ ቁ. 916/2008 ስራ አስፈጻው ራሱ ስልጣን ሰጪ ራሱ ተቀባይ እንዲሆን በማድረግ ህግ አውጭውን ‘ከተወካዮች ም/ቤት ወደ ወካዮች ም/ቤት’ አሳንሰውታል፡፡የአስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት
ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲፈጠር መፍትሔ የመሻት ቀዳሚ ኃላፊነት የተጣለባቸው በየዘርፉ የተቋቋሙት የአስተዳደር መ/ቤቶች ናቸው፡፡ ከትምህርት አሰጣጥ ወይም ጥራት ጋር የተያያዘ ወይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ሲከሰት የትምህርት ሚኒስቴር እንቅስቃሴ ይጀምራል፡፡ በጉምሩክ ህግ አፈጻጸም አቤቱታዎች ሲጎርፉ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መፍትሔ ያፈላልጋል፡፡ በግንባታ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ጉዳት ሲደርስባቸው የሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ላይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ትኩረት ሰጥቶ ስራ ይጀምራል፡፡ ችግሮችን ለመቅረፍ መላ መዘየድ ችግር የለውም፤ እንዲያውም ይበረታታል፡፡ይሁን እንጂ በአንድ አገር ውስጥ በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮች ሊቀረፉ የሚገባው በህግና በህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ከፊል ጉዳዮች የተወካዮች ም/ቤትን ጣልቃ ገብነት ይሻሉ፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች ችግር ፈቺነት በህግ ከተፈቀደላቸው ስልጣን በላይ ሊለጠጥ አይችልም፡፡ አዋጅ ሊመልሰው የሚገባውን መመሪያ ከቀደመው መ/ቤቶች ችግር ፈቺ መሆናቸው ቀርቶ ችግር ፈጣሪ ይሆናሉ፡፡ የአስተዳደር ድንጋጌዎች መመዘኛ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ህጋዊነት ነው፡፡ የቄሳርን ለቄሳር እንዲሉ ተወካዮች ሊመክሩበትና ሊፈቱት የሚገባውን ችግር ተሿሚዎች በመመሪያ ለመቅረፍ መሽቀዳደም የለባቸውም፡፡ ከላይ የቀረበውን ሀሳብ በተጨባጭ የሚያሳዩ ጥቂት አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ይጠቀሳሉ፡፡




















































































































































































































