WELCOME TO MY BLOG WEBSITES! This blog is for individuals and private organizations who want to read the FDRE Constitution as well as the interpretations of the Constitution as well as various laws of our country, various proclamations, government-approved directives, teachings and publications. Laws and the Constitution of our country. It is a website where we volunteer to help the public learn about draft laws and interpretations of the constitution.
Search This Blog
Nov 25, 2020
Nov 10, 2020
Nov 5, 2020
ፈቃደ ስልጣን
Discretion ወይም Discretionary Power ለሚለው ቃል ትክክለኛ ምትክ የአማርኛ ቃል ማግኘት ያዳግታል፡፡ በአማርኛ ‘ስልጣን’ ስንል በእንግሊዘኛው አራት የተለያየ መጠሪያ ካላቸው ቃላት መካከል አንደኛውን ወይም ሌላኛውን ማለታችን ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ‘ስልጣን’ የሚለው የአማርኛ ቃል Power, Discretion, Jurisdiction ወይም Authority ለሚሉት የእንግሊዝኛ ቃላት ወካይ ነው፡፡ Discretion ቁርጥ ያለ የአማርኛ ፍቺ የለውም፡፡ ስለሆነም ወደ ትርጓሜ ከመሄዳችን በፊት ወካይ ቃል ልንፈልግለት ይገባል፡፡ ከይዘቱ አንጻር Discretion እና ‘አማራጭ ስልጣን’ እንደ አቻ ፍቺ ብንወስዳቸው ያስኬዳል፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓይነት ስልጣን ከተለያዩ ተግባራት መካከል አንዱን ወይም ሌላኛውን ለመፈጸም ምርጫ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ‘አማራጭ ስልጣን’ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ፈጽሞ አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን Discretion ሰፊና የተለጠጠ የስልጣን ዓይነት የመሆኑን እውነታ ፍንትው አድርጎ አያሳይም፡፡
አዲስ የአማርኛ ቃል መፍጠር አስቸጋሪ እንደመሆኑ ግልጋሎት ላይ ከዋሉ የተለመዱ ቃላት መካከል ተቀራራቢውን መምረጥ ግድ ይላል፡፡ በዚህ መሰረት discretion የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በአግባቡ ሊገልጸው የሚችል የአማርኛ ቃል ‘የበዘፈቀደ ስልጣን’ ነው፡፡ በእርግጥ ‘በዘፈቀደ’ ሲባል የተለመደው ትርጉሙ አንዳችም ዓይነት ስርዓትና አካሄድ ያልተከተለ (arbitrary) ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሉታዊ ጎኑን ብቻ ያጎላዋል፡፡ ይሁን እንጂ በጥሬ ትርጉሙ ‘በዘፈቀደ’ ማለት እንደፈቀደ፣ እንደወደደ፣ እንዳሻው ማለት ነው፡፡ discretionary power በእርግጥም ‘የእንደፈቀደ፣ የእንደወደደ፣ የእንዳሻው ስልጣን’ ነው፡፡ ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር በዘፈቀደ የሚለው ቃል ተመራጭ የሚያደርገው ከገላጭነቱ አንጻር ብቻ ሳይሆን discretionary Power አዎንታዊ ጥቅሙን እና አሉታዊ ጉዳቱን አንድ ላይ ጠቅልሎ የሚይዝ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ‘በዘፈቀደ’ በበጎ ጎኑ በመግባባያነት ውሎ ስላማያውቅ እዚህ ላይ መጠቀሙ አንባቢን ማደናገሩ አይቀርም፡፡ ስለሆነም የውሳኔ ሰጭውን የተለጠጠ ፈቃድ እና ምርጫ በሚያንጸባርቅ መልኩ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ‘ፈቃደ ስልጣን’ የእንግሊዝኛውን discretion ወይም discretionary power እንዲወክል ተደርጓል፡፡
በቀጣይ ወደ ጽንሰ ሀሳቡ ዳሰሳ እናመራለን፡፡ ለመሆኑ ፈቃደ ስልጣን (discretion) ሲባል ምን ማለት ነው? ልኩና ገደቡስ የት ላይ ነው? በመደበኛነት ከሚታወቀው ስልጣን (Power) የሚለየውስ ምንድነው?
ፈቃደ ስልጣንን በጥልቀት በማጥናት በመስኩ ትልቅ አስዋጽኦ ካበረከቱ የአስተዳደር ህግ ሊቆች መካከል ስሙ በአንደኛነት የሚነሳለት ኬንዝ ከልፕ ዴቪስ (Kenneth Culp Davis) ፈቃደ ስልጣንን እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡፡
A public officer has discretion whenever the effective limits of his power leave him free to make a choice among possible causes of action and inaction.a
አንድ ባለስልጣን ፈቃደ ስልጣን አለው የሚባለው የስልጣኑ ገደብ ማድረግ ከሚችላቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል አንዱን ወይም ሌላኛውን የመምረጥ ነፃነት ሲኖረው ነው፡፡
ስለሆነም ፈቃደ ስልጣን ሲባል ውሳኔ ሰጪው አንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያለውን የምርጫ ወይም የፈቃድ ደረጃ ያመለክታል፡፡ በሌላ አነጋገር አንድን ድርጊት ለመፈፀም ወይም ላለመፈፀም ለውሳኔ ሰጪው የተሰጠው የመለጠጥ ነፃነት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በማናቸውም ከህግ በሚመነጭ ስልጣን (power) ውስጥ ደረጃው ቢለያይም የተወሰነ የመለጠጥ ነፃነት ይኖራል፡፡ ሆኖም የፈቃደ ስልጣንን ባህርያት ከመደበኛው በስነ-ስርዓትና በቅድመ ሁኔታ ከታጠረ ስልጣን (power) ጋር ብናነፃፅረው የተወሰነ ልዩነት እናያለን፡፡
ለንጽጽር እንዲረዳን በመጀመሪያ ፈቃደ ስልጣን በአንዳንድ ህጎች ላይ የተሰጠበትን መንገድ እናያለን፤
በብሔራዊ ዕጽዋት ዘር ኢንዱስትሪ ኤጀንሲ የሚመደብ የዘር ኢንስፔክተር አንድ ዘር የተደነገገ ዘር (የዕፅዋት ዘር አዋጅ ቁ 206/1992 ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚሆኑበት) መሆኑን እና የጥራት ደረጃውን ለመወሰን እንዲሁም ደግሞ በኤጀንሲው በተሰጠው ስልጣን መሰረት አስፈላጊ ነው ብሎ ላመነባቸው ለሌሎች ምክንያቶች የዘር ወይም የተክል ናሙናዎችን ለመውሰድ ይችላል፡፡b (ሰረዝ የተጨመረ)
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በግብይት ፈጻሚነት ዕውቅና ለማግኘት የሚፈልግ ሰው ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ማመልከቻ ማስገባት ያለበት ሲሆን ማመልከቻው በባለስልጣኑ መመሪያ መሰረት በተዘጋጀው ቅጽና የአቀራረብ ስርዓት መሰረት ባለስልጣኑ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን መረጃዎችና ፍሬ ነገሮች አካቶ መቅረብ ይኖርበታል፡፡c (ሰረዝ የተጨመረ)
የቴሌኮሙኒኬሽን ድርጅት የመስመር ዝርጋታ፤ ጥገና ወይም ተዛማጅ ተግባራትን ለማከናወን ወደ ማንኛውም መሬት መግባት እንዲሁም በመስመር ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ዛፍ ካለ መቁረጥ የሚችል ሲሆን የመሬቱ ባለይዞታ ተቃውሞ ካለው ለኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ አቤቱታ የማቅረብ ዕድል ተሰጥቶታል፡፡ ኤጀንሲው ለድርጅቱ እና ለባለይዞታው የመሰማት ዕድል በመስጠት ተቃውሞውን ከመረመረ በኋላ ተቃውሞውን ለመቀበል ወይም የታቀደው ተግባር ያለአንዳች ገደብ ወይም ተገቢ መስሎ የታየውን ገደብ በማድረግ እንዲከናወን ሊፈቅድ ይችላል፡፡d (ሰረዝ የተጨመረ)
የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ቦርድ በማናቸውም ፍርድ ቤቶች በሚሰራባቸው የሥነ-ሥርዓትና የመረጃ አቀራረብ ደንቦች ሳይወሰን የተሻለ መስሎ በሚታየው ማናቸውም ዘዴ ሊጠቀም ይችላል፡፡e (ሰረዝ የተጨመረ)
‘አስፈላጊ ነው ብሎ ላመነባቸው’፣ ‘አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን’፣ ‘ተገቢ መስሎ የታየውን’ በሚል አገላለጽ የሚሰጡ ስልጣናት ለአስተዳደር ህግ የራስ ምታት ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን አሰጣጥ ከዜጐች መብትና ነፃነት አንጻር አደጋው የከፋ፣ አስጊና አሳሳቢ ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በአግባቡ ካልተገራ በስተቀር ፈቃደ ስልጣን ወደ ሙስና እና ብልሹ አስተዳደር የማምራት አዝማሚያው ከፍ ያለ ነው፡፡
አደጋውና ስጋቱ ቢኖርም በህዝብ አስተዳደር ውስጥ ፈቃደ ስልጣን አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሁልጊዜ ስልጣንን እንደ ቁና እየሰፈሩ በልክ መስጠት በውጤታማ አስተዳደር ላይ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመወሰዱ በፊት ሊሟሉ የሚገባቸውን ስነ-ስርዓቶችና ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ በከፊልም ቢሆን የስልጣን አለአግባብ መገልገልን በህግ የቁጥጥር ማእቀፍ ስር ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ህግ አውጭው ስፋትና ጥልቀቱን በውል ለይቶ ያላወቀውን ችግር በአግባቡ ለመፍታት በተለዋዋጭ ችግሮች ልክ የሚለጠጥ ፈቃደ ስልጣን ያስፈልጋል፡፡ በህጉ ላይ በዝርዝር ሊዳሰሱ የማይችሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጊዜና ወቅቱን የጠበቀ አግባብ ያለው የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚችለው ውሳኔ ሰጪው አካል በሚለጠጡት ሁኔታዎች ልክ ተለጣጭ ስልጣን ሲሰጠው ነው፡፡
አስተዳደራዊ ስልጣን
አስተዳደራዊ ስልጣን
ደንብና መመሪያ ማውጣት እንዲሁም የአስተዳደር ውሳኔ እና እርምጃ መውሰድ ህግ አስፈፃሚ አካላት ህግና ፖሊሲን ለመተግበር የሚያከናውኗቸው ተግባራት ናቸው
አስተዳደራዊ ስልጣን
ደንብና መመሪያ ማውጣት እንዲሁም የአስተዳደር ውሳኔ እና እርምጃ መውሰድ ህግ አስፈፃሚ አካላት ህግና ፖሊሲን ለመተግበር የሚያከናውኗቸው ተግባራት ናቸው፡፡ የእነዚህ አካላት ዋነኛ ስልጣንና ተግባር ህግ ማውጣት አሊያም ዳኝነት መስጠት ሳይሆን ማስተዳደር ነው፡፡ አስተዳደራዊ ስልጣን ከህግ ማውጣት እና ዳኝነት መስጠት ውጪ ያሉትን ተግባራት በሙሉ ያጠቃልላል፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ይህን የእለት ተእለት የአስተዳደር ስራ በማከናወን ነው፡፡
በዚህ ስልጣን ስር ከሚወድቁ በርካታ ምሳሌዎችን መካከል ሪፖርት ማቅረብ፣ ፓስፖርት መስጠት፣ ፍቃድ መስጠት፣ ማደስ፣ ፀጥታ ማስከበር፣ ክስ መመስረት፣ እድገትና ሹመት መስጠት፣ ምርመራ፤ ቁጥጥርና ክትትል ማካሄድ የምክር ሀሳብ መስጠት ወዘተ ሁሉም የአስተዳደር መ/ቤቶች አስተዳደራዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም የሚያከናውኗቸው ስራዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ተግባራት የህግ መጣስ መኖርን አለመኖሩን ለማረጋገጥ መረጃ በመሰብሰብና በማጠናቀር ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የመረጃ አሰባሰብና ጥንቅር ስርዓት የንግድ ድርጅቶች በየጊዜው በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ሊመሰረት ይችላል፡፡ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የመረጃ አሰባሰብ ስርዓቱ በአካል ተገኝቶ ቀጥተኛ እና የአካባቢ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ እና የማጣራት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡
የመርማሪነት ስራ ህጉ ልዩ ስልጣን በሰጣቸው መርማሪዎች የሚከናወን ሲሆን የምርመራ ሂደቱም በህግ ማእቀፍ ውስጥ ይመራል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የፖሊስ የምርመራ ተግባር ነው፡፡ ፖሊስ ወንጀል ሲፈጸም ወይም ተፈጽሟል የሚል መረጃ ከደረሰው አሊያም ተገቢ ጥርጣሬ ካደረበት የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ በአካል በመገኘት ተጨባጭ ማስረጃዎችን የመሰብሰብ እና ተጠርጣሪውን የመመርመር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ረገድ ሰፊ ስልጣናት አሉት፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የአስተዳደር መ/ቤቶች የመርማሪነት፣ የቁጥጥርና ክትትል ስልጣን በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ ለፖሊስ ከተሰጠው ስልጣን ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡
በአስረጂነት በተወሰኑ ህጎች ለተቆጣጠሪዎች የተሰጣቸው መጠነ ሰፊ ስልጣን በማጣቀሻነት እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
ሳያሳውቁ ወይም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይዙ በማንኛውም ተገቢ መስሎ በሚታያቸው ጊዜ ወደ ማንኛውም ቦታ ወይም ቅጥር ግቢ መግባት
ማንኛውንም ሰው ብቻውን ወይም በምስክር ፊት የመጠየቅ
ከብክለት ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ወረቀት፣ ማህደር ወይም ሌላ ሰነድ መፈተሽ፣ መገልበጥ ወይም ለይቶ መቅዳት
የማንኛውንም ቁስ ናሙናዎች እንደአስፈላጊነቱ ያለክፍያ መውሰድና በአካባቢ ወይም በህይወት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ አለመሆኑን ለመወሰን መመርመር ወይም ማስመርመር
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁ. 300/1995 ወይም ሌላ ህግ መከበሩን ለማረጋገጥ ሸቀጥን፣ የአመራረት ሂደትን ወይም መገልገያን በፍቶግራፍ ማንሳት፣ መለካት፣ መሳል ወይም መፈተሽ
አዋጁን ወይም አግባብ ያለውን ሌላ ህግ በመተላለፍ ጥፋት ተፈጽሞበታል የተባለ መሳሪያን ወይም ሌላ ነገርን መያዝ
ሕግን በመተላለፍ በይዞታ ስር የተደረጉ የዱር እንስሳት ወይም የዱር እንስሳት ውጤቶች ተደብቀዋል ብሎ ለማመን በቂ ምክንያት ሲኖር ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ወደ ማንኛውም ሰው መሬት፣ ህንጻ፣ ድንኳን፣ ተሸከርካሪ፣ የአየር መንኮራኩር ወይም ጀልባ ውስጥ የመግባትና የመፈተሸ እንዲሁም ሻንጣ ወይም እሽግ የመፈተሸ
ሕግን በመተላለፍ በይዞታ ስር የተደረጉ የዱር እንስሳት ወይም የዱር እንስሳት ውጤቶችን እንዲሁም ጥፋቱ የተፈጸመባቸውን መሳሪያዎች እንዲወረሱ ለማድረግ እንዲቻል በቁጥጥር ስር የማድረግና የሚመለከተው አካል ባወጣው የመመዝገቢያ ቅፅ መሰረት ተገቢውን ደረሰኝ ሰጥቶ የመረከብ
የዱር እንስሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ማፅደቂያ አዋጅ ቁ. 541/1999 አንቀጽ 16 ድንጋጌዎች በመተላለፍ ጥፋት ሲፈጽም የተገኘን ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዞ ለሚመለከተው ህግ አስከባሪ አካል ማስረከብ
የደን ውጤቶችን የጫነ ወይም ለመጫኑ የሚጠረጠርን ማናቸውንም ማጓጓዣ በደን መግቢያና መውጫዎች እንደአስፈላጊነቱ በሚመረጡ የሀገር ውስጥ እና የድንበር መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ አስቁሞ መፈተሸ
የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁ. 542/1999 በመተላለፍ ተዘጋጅተው ሲጓጓዙ ወይም ተከማችተው የተገኙ የደን ውጤቶችን ከድርጊቱ ተጠያቂዎች ጋር የመያዝ
የቡና ጥራት ቁጥጥርና ግብይት አዋጅ ቁ. 602/2000 ለማስፈጸም የሚወጡ ደንብና መመሪያዎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ ቡና ሊገኝበት ይችላል ተብሎ የሚገመትን መጋዘን፣ መኖሪያ ቤት፣ የመንግስት ድርጅት፣ ማጓጓዣ ወይም ማናቸውም ሌላ ቦታ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የመፈተሽ፣ህገ ወጥ ቡና ሲያዝ የማሸግ፣ ምርቱን የማገድ፣ የመያዝ፣ ህገ ወጥነታቸው የማያጠራጥር ሲሆን የቡናው ባለቤት ለፍርድ ቤት ቅሬታ የማቅረብ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የመውረስና የመሸጥ.
Subscribe to:
Posts (Atom)
PDF DOCUMENTS AND FILE
WordPress
WELCOME TO MUHAJER SEMAN SURAFEL WEBSITES HOME ON WORDPRESS

This blog is for individuals and private organizations who want to read the FDRE Constitution as well as the interpretations of the Constitution as well as various laws of our country, various proclamations, government-approved directives, teachings and publications. Laws and the Constitution of our country. It is a website where we volunteer to help the public learn about draft laws and interpretations of the constitution




















































































































































































































