Discretion ወይም Discretionary Power ለሚለው ቃል ትክክለኛ ምትክ የአማርኛ ቃል ማግኘት ያዳግታል፡፡ በአማርኛ ‘ስልጣን’ ስንል በእንግሊዘኛው አራት የተለያየ መጠሪያ ካላቸው ቃላት መካከል አንደኛውን ወይም ሌላኛውን ማለታችን ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ‘ስልጣን’ የሚለው የአማርኛ ቃል Power, Discretion, Jurisdiction ወይም Authority ለሚሉት የእንግሊዝኛ ቃላት ወካይ ነው፡፡ Discretion ቁርጥ ያለ የአማርኛ ፍቺ የለውም፡፡ ስለሆነም ወደ ትርጓሜ ከመሄዳችን በፊት ወካይ ቃል ልንፈልግለት ይገባል፡፡ ከይዘቱ አንጻር Discretion እና ‘አማራጭ ስልጣን’ እንደ አቻ ፍቺ ብንወስዳቸው ያስኬዳል፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓይነት ስልጣን ከተለያዩ ተግባራት መካከል አንዱን ወይም ሌላኛውን ለመፈጸም ምርጫ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ‘አማራጭ ስልጣን’ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ፈጽሞ አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን Discretion ሰፊና የተለጠጠ የስልጣን ዓይነት የመሆኑን እውነታ ፍንትው አድርጎ አያሳይም፡፡
አዲስ የአማርኛ ቃል መፍጠር አስቸጋሪ እንደመሆኑ ግልጋሎት ላይ ከዋሉ የተለመዱ ቃላት መካከል ተቀራራቢውን መምረጥ ግድ ይላል፡፡ በዚህ መሰረት discretion የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በአግባቡ ሊገልጸው የሚችል የአማርኛ ቃል ‘የበዘፈቀደ ስልጣን’ ነው፡፡ በእርግጥ ‘በዘፈቀደ’ ሲባል የተለመደው ትርጉሙ አንዳችም ዓይነት ስርዓትና አካሄድ ያልተከተለ (arbitrary) ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሉታዊ ጎኑን ብቻ ያጎላዋል፡፡ ይሁን እንጂ በጥሬ ትርጉሙ ‘በዘፈቀደ’ ማለት እንደፈቀደ፣ እንደወደደ፣ እንዳሻው ማለት ነው፡፡ discretionary power በእርግጥም ‘የእንደፈቀደ፣ የእንደወደደ፣ የእንዳሻው ስልጣን’ ነው፡፡ ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር በዘፈቀደ የሚለው ቃል ተመራጭ የሚያደርገው ከገላጭነቱ አንጻር ብቻ ሳይሆን discretionary Power አዎንታዊ ጥቅሙን እና አሉታዊ ጉዳቱን አንድ ላይ ጠቅልሎ የሚይዝ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ‘በዘፈቀደ’ በበጎ ጎኑ በመግባባያነት ውሎ ስላማያውቅ እዚህ ላይ መጠቀሙ አንባቢን ማደናገሩ አይቀርም፡፡ ስለሆነም የውሳኔ ሰጭውን የተለጠጠ ፈቃድ እና ምርጫ በሚያንጸባርቅ መልኩ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ‘ፈቃደ ስልጣን’ የእንግሊዝኛውን discretion ወይም discretionary power እንዲወክል ተደርጓል፡፡
በቀጣይ ወደ ጽንሰ ሀሳቡ ዳሰሳ እናመራለን፡፡ ለመሆኑ ፈቃደ ስልጣን (discretion) ሲባል ምን ማለት ነው? ልኩና ገደቡስ የት ላይ ነው? በመደበኛነት ከሚታወቀው ስልጣን (Power) የሚለየውስ ምንድነው?
ፈቃደ ስልጣንን በጥልቀት በማጥናት በመስኩ ትልቅ አስዋጽኦ ካበረከቱ የአስተዳደር ህግ ሊቆች መካከል ስሙ በአንደኛነት የሚነሳለት ኬንዝ ከልፕ ዴቪስ (Kenneth Culp Davis) ፈቃደ ስልጣንን እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡፡
A public officer has discretion whenever the effective limits of his power leave him free to make a choice among possible causes of action and inaction.a
አንድ ባለስልጣን ፈቃደ ስልጣን አለው የሚባለው የስልጣኑ ገደብ ማድረግ ከሚችላቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል አንዱን ወይም ሌላኛውን የመምረጥ ነፃነት ሲኖረው ነው፡፡
ስለሆነም ፈቃደ ስልጣን ሲባል ውሳኔ ሰጪው አንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያለውን የምርጫ ወይም የፈቃድ ደረጃ ያመለክታል፡፡ በሌላ አነጋገር አንድን ድርጊት ለመፈፀም ወይም ላለመፈፀም ለውሳኔ ሰጪው የተሰጠው የመለጠጥ ነፃነት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በማናቸውም ከህግ በሚመነጭ ስልጣን (power) ውስጥ ደረጃው ቢለያይም የተወሰነ የመለጠጥ ነፃነት ይኖራል፡፡ ሆኖም የፈቃደ ስልጣንን ባህርያት ከመደበኛው በስነ-ስርዓትና በቅድመ ሁኔታ ከታጠረ ስልጣን (power) ጋር ብናነፃፅረው የተወሰነ ልዩነት እናያለን፡፡
ለንጽጽር እንዲረዳን በመጀመሪያ ፈቃደ ስልጣን በአንዳንድ ህጎች ላይ የተሰጠበትን መንገድ እናያለን፤
በብሔራዊ ዕጽዋት ዘር ኢንዱስትሪ ኤጀንሲ የሚመደብ የዘር ኢንስፔክተር አንድ ዘር የተደነገገ ዘር (የዕፅዋት ዘር አዋጅ ቁ 206/1992 ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚሆኑበት) መሆኑን እና የጥራት ደረጃውን ለመወሰን እንዲሁም ደግሞ በኤጀንሲው በተሰጠው ስልጣን መሰረት አስፈላጊ ነው ብሎ ላመነባቸው ለሌሎች ምክንያቶች የዘር ወይም የተክል ናሙናዎችን ለመውሰድ ይችላል፡፡b (ሰረዝ የተጨመረ)
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በግብይት ፈጻሚነት ዕውቅና ለማግኘት የሚፈልግ ሰው ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ማመልከቻ ማስገባት ያለበት ሲሆን ማመልከቻው በባለስልጣኑ መመሪያ መሰረት በተዘጋጀው ቅጽና የአቀራረብ ስርዓት መሰረት ባለስልጣኑ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን መረጃዎችና ፍሬ ነገሮች አካቶ መቅረብ ይኖርበታል፡፡c (ሰረዝ የተጨመረ)
የቴሌኮሙኒኬሽን ድርጅት የመስመር ዝርጋታ፤ ጥገና ወይም ተዛማጅ ተግባራትን ለማከናወን ወደ ማንኛውም መሬት መግባት እንዲሁም በመስመር ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ዛፍ ካለ መቁረጥ የሚችል ሲሆን የመሬቱ ባለይዞታ ተቃውሞ ካለው ለኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ አቤቱታ የማቅረብ ዕድል ተሰጥቶታል፡፡ ኤጀንሲው ለድርጅቱ እና ለባለይዞታው የመሰማት ዕድል በመስጠት ተቃውሞውን ከመረመረ በኋላ ተቃውሞውን ለመቀበል ወይም የታቀደው ተግባር ያለአንዳች ገደብ ወይም ተገቢ መስሎ የታየውን ገደብ በማድረግ እንዲከናወን ሊፈቅድ ይችላል፡፡d (ሰረዝ የተጨመረ)
የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ቦርድ በማናቸውም ፍርድ ቤቶች በሚሰራባቸው የሥነ-ሥርዓትና የመረጃ አቀራረብ ደንቦች ሳይወሰን የተሻለ መስሎ በሚታየው ማናቸውም ዘዴ ሊጠቀም ይችላል፡፡e (ሰረዝ የተጨመረ)
‘አስፈላጊ ነው ብሎ ላመነባቸው’፣ ‘አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን’፣ ‘ተገቢ መስሎ የታየውን’ በሚል አገላለጽ የሚሰጡ ስልጣናት ለአስተዳደር ህግ የራስ ምታት ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን አሰጣጥ ከዜጐች መብትና ነፃነት አንጻር አደጋው የከፋ፣ አስጊና አሳሳቢ ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በአግባቡ ካልተገራ በስተቀር ፈቃደ ስልጣን ወደ ሙስና እና ብልሹ አስተዳደር የማምራት አዝማሚያው ከፍ ያለ ነው፡፡
አደጋውና ስጋቱ ቢኖርም በህዝብ አስተዳደር ውስጥ ፈቃደ ስልጣን አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሁልጊዜ ስልጣንን እንደ ቁና እየሰፈሩ በልክ መስጠት በውጤታማ አስተዳደር ላይ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመወሰዱ በፊት ሊሟሉ የሚገባቸውን ስነ-ስርዓቶችና ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ በከፊልም ቢሆን የስልጣን አለአግባብ መገልገልን በህግ የቁጥጥር ማእቀፍ ስር ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ህግ አውጭው ስፋትና ጥልቀቱን በውል ለይቶ ያላወቀውን ችግር በአግባቡ ለመፍታት በተለዋዋጭ ችግሮች ልክ የሚለጠጥ ፈቃደ ስልጣን ያስፈልጋል፡፡ በህጉ ላይ በዝርዝር ሊዳሰሱ የማይችሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጊዜና ወቅቱን የጠበቀ አግባብ ያለው የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚችለው ውሳኔ ሰጪው አካል በሚለጠጡት ሁኔታዎች ልክ ተለጣጭ ስልጣን ሲሰጠው ነው፡፡




















































































































































































































