የተፈጻሚነቱ ወሰን
የአስተዳደር ህግ የመንግስትንና የግለሰብ ግንኙት በሚገዛው የህዝብ አስተዳደር ህግ (Public law) ውስጥ ይመደባል፡፡ ይህም ማለት በሁለት ግለሰቦች ወይም በንግድ ድርጅቶች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ በተጨማሪም ሁሉም በመንግስት እና ግለሰብ መካከል የሚፈጠር ግንኙነት በአስተዳደር ህግ ውስጥ አይወድቅም፡፡ ተፈጻሚነቱ የአስተዳደር አካላት በህግ የተሰጣቸውን ስልጣንና ግዴታ ተጠቅመው ህዝባዊ ተግባራት በሚያከናውኑበት ጊዜ ነው፡፡ ከህግ አውጭው የተሰጣቸውን ውክልና ተጠቅመው ደንብና መመሪያ ሲያወጡ እንዲሁም የግለሰቦችን መብትና ጥቅም የሚነካ አስተዳደራዊ ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ ለአስተዳደር ህግ መርሆዎች ተገዢ ሊሆኑ ይገባል፡፡ አንድ መስሪያ ቤት ባወጣው መመሪያ ወይም በወሰደው የአስተዳደር ውሳኔ ምክንያት የሚነሳ ክርክር በአስተዳደር ህግ የሚመራ የአስተዳደር ክርክር ነው፡፡
ከዚህ በተለየ መልኩ ከግለሰቦች ወይም ከድርጅቶች ጋር በሚመሰርቱት የውል ግንኙነት ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው መደበኛው የውል ህግ እንጂ የአስተዳደር ህግ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ የውሉ አይነት በአስተዳደር ውል ውስጥ የሚመደብ ከሆነ የተለዩ የውል ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የኃላፊነታቸው ምንጭ በውል ላይ ካልተመሰረተ ተጠያቂነታቸው የሚወሰነው ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነትን በሚገዙት የፍትሐብሔር ድንጋጌዎች ነው፡፡
ሌላው ከተፈፃሚነት ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ህጉ የሚያካትታቸወ ውሳኔ ሰጪ አካላት የትኞቹ ናቸው? የሚለው ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ማለት አስተዳደር የሚመራበት ህግ እንደመሆኑ ፓርላማው በህግ አውጪነት ስልጣኑ በሚያወጣቸው ህጎች ወይም በሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እንዲሁም ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ስልጣናቸው በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ መከላከያ ሰራዊትን የሚመለከቱ ጉዳዮችም ከዚህ ህግ ማእቀፍ ውጭ ናቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአስተዳደር ህግ ከአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ባሻገር ብቸኛ አገልግሎት አቅራቢ የሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች (Public Corporations) ከደንበኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይም ተፈፃሚነት እያገኘ ነው፡፡ አንድ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ከኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ጋር ያለው ግንኙነት ምንም እንኳን በውል ላይ የተመሰረተ ቢሆንም አገልግሎቱን ከማግኘት መብት ጀምሮ እስከ አገልግሎቱ መቋረጥ ድረስ በድርጅቱ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከምንም በላይ ፍትሐዊነታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ድርጅቱ በዋጋ አተማመን እና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚያደርጋቸው ማሻሻያዎችና ይህንን ተከትሎ የሚያወጣቸው የአሰራር ደንቦችና መመሪያዎች ለራሱ ለብቻው የሚተዉ ሳይሆን በህግ በተለይም በአስተዳደር ህግ ደንቦች መመራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው የመንግስት ልማት ድርጅቶች እንደ ነጋዴ ድርጅት መታየት የሌለባቸው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የመንግስት ቤቶችን የሚያስተዳድሩት የቀበሌ መስተዳድር እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሁለቱም ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በተራ ውል ብቻ የተመሰረተ ቢመስልም ከዚህ ባለፈ በመንግስትና ግለሰብ ግንኙነት ማዕቀፍ ውስጥ መታየት አለበት፡፡ የመንግስት ቤቶችን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽንa ‘እንደማንኛውም ባለሃብት ቤቶቹን ለፈለገው ሰው የማከራየት ሕጋዊ መብት’b የለውም፡፡ ይልቅስ በህግ የተቋቋመበትን የቤት እጥረት የማቃለል ዓላማ፤
..ለማሳካት የሚችሉ ግልፅ የአሠራር ሥርዓቶችን በመቀየስ የቤት ኪራይ ግልጋሎት የሚሰጥባቸውን መመዘኛዎች በማውጣት መመዘኛውን ለሚያሟሉ ሰዎች በቅደም ተከተል ክፍት ቤት ሲኖረው የማስተናገድ ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡’c
ስለሆነም መንግስት ለዜጎቹ በሚያቀርባቸው አገልግሎቶች የሂደቱን ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ በእርግጥ የአስተዳደር ህግ ተፈፃሚነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሆነ የቀበሌ መስተዳድር አገልግሎታቸውን ለማቋረጥ በቂ የህግ ምክንያት ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ከመሆኑም በላይ ውሳኔያቸው ከህገ መንግስቱ የዜጐች መጠለያ የማግኘት መብት አንጻር መቃኘት ይኖርበታል፡፡
በመጨረሻ የተፈጻሚነት ወሰኑ ከአስተዳደራዊ ውሳኔ ይዘትና ሂደት አንጻር የራሱ ገደብ እንዳለበት መገንዘብ ያሻል፡፡ አስተዳደር ህግ አካሄድን እንጂ ይዘትን የሚመለከት ህግ አይደለም፡፡ ትኩረቱ ደንብና መመሪያው እንዴት ወጣ? አስተዳደራዊ ውሳኔው እንዴት ተሰጠ? እንጂ የመመሪያው ወይም የውሳኔው ይዘት ትክክለኛ መሆን አለመሆን አይደለም፡፡ ድርጊቱ ትክክለኛ ነበረ ወይስ አልነበረም? የሚለው ጥያቄ ስለጉዳዩ በቂ እውቀት ላለው የአስተዳደር አካል የሚተው እንጂ በፍርድ ቤት ምላሽ የሚያገኝ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል በግብር አወሳሰን ወቅት በህግ ተለይተው የተቀመጡ የተለያዩ ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ የግብር ሰብሳቢው አካል የተወሰነ የገንዘብ መጠን ሊወስን ይችላል፡፡ የአስተዳደር ህግ የግብር አወሳሰኑን ህጋዊነት ወይም ፍትሐዊነት በተመለከተ ካልሆነ በስተቀር በእርግጥ የገንዘቡ መጠን ምን ያህል መሆን አለበት? የሚለውን ጥያቄ ለመዳሰስ ሆነ ለመመለስ ወሰኑ አይፈቅድለትም፡፡





















































































































































































































