የህጉ ምንጮች
የአስተዳደር ህግ የሚመራባቸው መርሆዎች እና ደንቦች ከተለያዩ ምንጮች ይገኛሉ፡፡
የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ የዛችን አገር ፖለቲካዊና ህገ-መንግስታዊ ስርዓትና አወቃቀር የሚያንጸባርቅና ከዚሁ አንጻር የተቀረጸ እንደመሆኑ እነዚህን ምንጮች ወጥ በሆነ መልኩ ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ ይሁን እንጂ ከአጠቀላይ ምልከታ በመነሳት ምንጮቹን እንደሚከተለው መዘርዘር ይቻላል፡፡
ህገ መንግሰት
የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ መልክና ቅርጽ ምን እንደሚመስል ለመረዳት መነሻችን የዛች አገር ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ነው፡፡ ብዙዎቹ የአስተዳደር ህግ መርሆዎች መሰረታቸው የተተከለው በህገ መንግስት ላይ ከመሆኑም በላይ ወሰንና አፈጻጸማቸው እንዲሁ ለብቻው ተነጥሎ የቆመ አይደለም፡፡ የአስተዳደር ህግ ተፈጻሚነት የሚያገኘው በህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡
aህግ
የመንግስት ስልጣን ዋነኛ ምንጩ በህግ አውጭው የሚወጣው ህግ ሲሆን በአስተዳደር ህግ ውስጥ በተለምዶ ‘ማቋቋሚያ አዋጅ’ ወይም ‘እናት ህግ’ እየተባለ ይጠራል፡፡ በአገራችን በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ በተዋቀረው ህግ አውጪ አካል የሚወጣው አዋጅ
b የአስተዳደር መስሪያ ቤቶችን ስልጣን በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ለይቶ ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም ይህ አዋጅ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ በጥልቀት ሊመረምርና ሊተነተን ይገባዋል፡፡
ህግ አውጪው ስልጣን ከመስጠት በተጨማሪ ስልጣኑ ተግባር ላይ የሚውልበትን መንገድና ስርዓት ይደነግጋል፡፡ በስልጣን መገልገል ሂደት ተፈጻሚ የሚሆነው ስነ-ስርዓት አብዛኛውን ጊዜ ስልጣን በሚሰጠው አዋጅ ላይ ይካተታል፡፡ በሌላ መልኩ ህግ አውጪው በሁሉም ስልጣን በተሰጣቸው አካላት ላይ በጠቅላላው ተፈጻሚ የሚሆን ወጥ ደንብ በማስቀመጥ ሁሉን አቀፍ ስርዓት ሊዘረጋ ይችላል፡፡
በዚህ ረገድ በአሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም የወጣው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ደንብ (Administrative Procedure Act) ተጠቃሽ ነው፡፡ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ ተፈጻሚ የሚሆኑ ደንቦችና ስርዓቶች አስገዳጅነት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን ስነ-ስርዓቱን የሚጥስ ውሳኔ ጸንቶ የሚቆምበት የህግ መሰረት አይኖርም፡፡ በአጠቃላይ የስልጣን ምንጭ የሚወሰንበት መንገድ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡
ደንብና መመሪያ
በአገራችን በተለይም በፌደራል መንግስቱ ደረጃ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የተለያዩ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በውክልና በሚተላለፍላቸው ስልጣን መሰረት ደንብና መመሪያ ያወጣሉ፡፡ የእነዚህ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች አወጣጥ ስርዓት እንዲሁም ህጋዊነታቸውና ህገ መንግስታዊነታቸው የሚረጋገጥበት መንገድ በህጉ አብይ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በእርግጥ የእያንዳንዱ ደንብና መመሪያ ይዘት ከአስተዳደር ህግ ጥናት ወሰን ውጭ ነው፡፡ ህጉ እንደ ስልጣን መቆጣጠሪያ መሳሪያነቱ ደንብና መመሪያ በህግ በተቀመጠው የስልጣን ገደብ ውስጥ ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ መውጣቱን ማረጋገጥ አይነተኛ ዓላማው ነው፡፡ በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን በአስተዳደር ህግ ውስጥ ያለው ቦታ መቃኘት ያለበትም ከዚሁ ነጥብ አንፃር ነው፡፡ ለህጋዊነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ደንብና መመሪያው ላይ አስገዳጅ ውጤት ኖሯቸው የተደነገጉት ጉዳዮች ስልጣን በሰጠው አዋጅ ስር የተሸፈኑ መሆናቸውን መመርመርን ይጠይቃል፡፡
የፍርድ ቤት ውሳኔዎች
መደበኛ ፍ/ቤቶች የስልጣን መገልገልን ህጋዊነትና ፍትሐዊነት በመቆጣጠር ለግለሰቦች መብትና ነፃነት መጠበቅ የሚያበረክቱ አስተዋጽኦ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ ፍ/ቤቶች አስተዳደሩ በህግ እንዲመራ እና ለህጋዊነት መርህ ተገዢ እንዲሆን በተጨማሪም በህግ የተሰጠውን ስልጣን በፍትሀዊ መንገድ እንዲገለገል የተለያዩ መለኪያዎችንና መስፈርቶችን በማስቀመጥ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ህገ-መንግስታዊ ሚናቸው የመልካም አስተዳደር እሴቶች ገንቢ ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የፌደራል እና የክልል መደበኛ ፍርድ ቤቶች በአስተዳደራዊ ክርክር የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ለአስተዳደር ህግ ጥናት ግብዓት ናቸው፡፡ በተለይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም በመላ አገሪቱ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ያለው እንደመሆኑ የአስተዳደር ህግን ተግባራዊ አፈጻጸም ለመመዘን ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ከመደበኛ ፍ/ቤቶች በተጨማሪ በአስተዳደር ተቋማት ውስጥ ወይም ለብቻቸው ገለልተኛ ሆነው የሚቋቋሙት በተለምዶ ‘የአስተዳደር ፍ/ቤት’ በሚል የሚታወቁት የአስተዳደር ጉባዔዎች (Administrative Tribunals) የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ እና የአስተዳደር ፍትህ ምን እንደሚመስልና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት አጋዥ ምንጮች ናቸው፡፡
ያም ሆኖ የመደበኛ ፍ/ቤት ሆነ የአስተዳደር ጉባዔዎች ውሳኔዎች በአስተዳደር ህግ ውስጥ ያላቸው ቦታ ውስን ነው፡፡ በየአስተዳደር መስሪያ ቤቱ በየጊዜው በሚሰጡት ውሳኔዎችና በሚወጡት ደንብና መመሪያዎች አማካይነት በዜጋው ላይ የሚፈጸሙት በደሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቢሆንም የፍ/ቤትን ደጃፍ የሚረግጡት ግን በጣት የሚቆጠሩት ናቸው፡ ከሚቀርቡት አቤቱታዎች መካከልም በተለያዩ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች የተነሳ ዳኝነት ሳይታይ አብዛኛዎቹ ወዲያውኑ ውድቅ ይደረጋሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ውሳኔዎቹ አጠቃላዩን የአስተዳደር ሂደት ባህርይ እና አካሄድ ገላጭ ወይም ወካይ ሊሆኑ አይችሉም፡፡