SUBSCRIBE

Search This Blog

Sep 26, 2020

የተሻሩና ተፈጻሚ የሚሆኑ ህጎች

በሽግግር ወቅት ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሠረት በመንግሥት ከሚያዙ የልማት ድርጅቶች በስተቀር ቀሪዎቹ በግል ባለሀብቶች ተሳትፎም ሆነ በሙሉ ባለቤትነት የሚመሩበትን ሥርዓት ማመቻቸት ተገቢ ስለሆነ፤

እነዚህን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ ስለመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዲስ ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ስለሆነ፤
በሽግግሩ ወቅት ቻርተር አንቀጽ 9(መ) መሠረት የሚከተለው ታውጆአል።
ክፍል 1
ጠቅላላ ድንጋጌዎች
አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።
ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ የተለየ ትርጓሜ የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፣
“ድርጅት” ማለት በመንግሥት ሙሉ ባለቤትነት የማምረት፣ የማከፋፈል፣ አገልግሎት የመስጠት ወይም ሌሎች የኢኮኖሚ ተግባሮችንና ከእነዚሁ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በንግድ መልክ ለማካሄድ በዚህ አዋጅ መሠረት የተቋቋመ የመንግሥት ድርጅት ነው፤
“ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን” ማለት የመንግሥት የባቤትነት መብትን ለማስከበር ሲባል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚሰይመው አካል ነው፤
“ጠቅላላ ንብረት” ማለት የድርጅት የማይንቀሳቀስና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ድርጅቱ ገና ያልተቀበላቸው ገቢዎች፣ ጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳብ ሲሆን ግዙፍ ያልሆኑ ንብረቶች በቅድሚያ የተከፈሉ ወጪዎችንና ሌሎች ገቢ መሆን ያለባቸው ሂሳቦችን ይጨምራል፤
“የተጣራ ጠቅላላ ንብረት” ማለት ከጠቅላላ ንብረት ላይ በተያዘው የሂሳብ ዓመት ውስጥ የሚከፈሉ ዕዳዎች በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ ዕዳወች በቅድሚያ የተከፈለ ገቢና ሌሎች ዕዳዎች ተቀንሰው የሚቀረው ንብረት ነው፤
“ካፒታል” ማለት አንድ ድርጅት በተቋቋመ ጊዜና ከዚያም በኋላ መንግሥት የሚመደብለት የተጣራ ጠቅላላ ንብረት በተመደበበት ጊዜ ያለው ዋጋ ነው፤
“ኦዲተር” ማለት በዚህ አዋጅ አንቀጽ 32 በተመለከተው መሠረት የማናቸውንም ድርጅት ሂሳብ የሚመረምር የተፈጥሮ ሰው ወይም የሕግ ሰውነት የተሰጠው አካል ነው፤
“የተጣራ ትርፍ” ማለት ከገቢዎችና ከሌሎች ክፍያዎች ከተገኘው ገንዘብ ላይ ወጪዎችና በሂሳብ ዓመቱ ውስጥ ለሥራ ማስኬጃና ደመወዝ ባግባቡ ወጪ የተደረጉ ሂሳቦች፣ የእርጅና ቅናሽ/ዲፕሪሼሽን/፣ ወለድና ልዩ ልዩ ታክሶች ተቀንሰው የሚቀረው ሂሳብ ነው፤
“መንግሥት” ማለት ማዕከላዊ መንግሥት ነው፣
“የመንግሥት የትርፍ ድርሻ” ማለት ከተጣራው ትርፍ ላይ ወደ ሕጋዊ መጠባበቂያ ሂሳብና ሌሎች መጠባበቂያ ሂሳቦች ገቢ የሚሆነው ገንዘብ ተቀንሶ የሚቀረው ሂሳብ ነው፣
“ቦርድ” ማለት በዚህ ዓዋጅ አንቀጽ 10/2/ እና አንቀጽ 12 መሠረት የሚቋቋም የድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ ነው።
የተሻሩና ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ሕጐች
የሚከተሉት በዚህ አዋጅ ተሽረዋል፣
የመንግሥት የልማት ሥራ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 20/1967፣
አንዳንድ የመንግሥት የልማት ሥራ ድርጅቶችን በአንዳንድ ሚኒስቴሮች ቁጥጥር ሥር ለማዋል የወጣው አዋጅ ቁጥር 131/1970፣
የመንግሥት የልማት ሥራ ድርጅቶች ደንብ ቁጥር 5/1967፣
የእርሻ ልማት ድርጅቶች ደንብ ቁጥር 60/1970፣
የሚከተሉት በድርጅቶች ላይ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፣
የመንግሥት ገንዘብ እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያና ማስተባበሪያ አዋጅ ቁጥር
163/1971፣
ይህን አዋጅ የሚቃረን ማናቸውም ሕግ፣ ደንብ መመሪያ ወይም የአሠራር ልምድ።
የሌሎች ሕጐች ተፈጻሚነት
በዚህ አዋጅ በሌላ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር አግባብነት ያላቸው የፍትሐብሔር ሕግና የንግድ ሕግ ድንጋጌዎች በድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ።
ክፍል 2
የድርጅት አመራረት የሕግ ሰውነትና ችሎታ
ድርጅት ከመቋቋሙ በፊት ሊሟሉ ስለሚገባቸው ሁኔታዎች
አንድ ድርጅት ከመቋቋሙ በፊት ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን፣
በዓይነት የተደረገ ክፍያ ካለ፣ ንብረቱ በባለሙያዎች በትክክል የተገመተ መሆኑን፤
በካፒታልነት የተከፈለ ጥሬ ገንዘብ ካለ በሚቋቋመው ድርጅት ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ተቀማጭ መሆኑን፣ ያረጋግጣል።
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1/ሀ/ የተደነገገው ቢኖርም በዓይነት የተደረገው ክፍያ በኦዲተር የተረጋገጠ ሂሳብ ያለው ከሆነ ግምቱ በሂሳብ መዝገቡ መሠረት ሊሆን ይችላል።
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1/ሀ/ የተመለከቱት ባለሙያዎች የንብረቱን ዝርዝር መግለጫ፣ ለእያንዳንዱ ንብረት የተሰጠውን ዋጋ እና የአገማመቱን ዘዴ የያዘ ሪፖርት ያዘጋጃሉ። ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን፣ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በሌላ ሕግ የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ሥራ ድርጅትን ሲያስተዳድር የነበረ አግባብ ያለው የመንግሥት መሥሪያ ቤትና ድርጅቱ እያንዳንዳቸው የሪፖርቱን አንድ ኮፒ ያገኛሉ።
ድርጅቱ ከመቋቋሙ በፊት ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ለድርጅቱ ምሥረታ ያደረገው ወጪ ካለና ይኸው በኦዲተር የተረጋገጠ ከሆነ ለድርጅቱ በካፒታልነት ይታሰባል።
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1/ለ/ የተመለከተው ገንዘብ የድርጅቱ ማቋቋሚያ ደንብ እስኪወጣ ድረስ ከባንክ ወጭ አይሆንም።
መመሥረቻ ሕግ
ማናቸውም ድርጅት የሚቋቋመው በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጣ ደንብ ይሆናል። በማቋቋሚያ ደንቡ የሚከተሉት ዝርዝር ጉዳዮች ይገለጻሉ፣
የድርጅቱ ስም፣
ድርጅቱ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚተዳደር መሆኑ፣
ድርጅቱ የተቋቋመባቸው ዓላማዎች፣
የተፈቀደው ካፒታል፣
በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የተከፈለው መነሻ ካፒታል መጠን፣
ድርጅቱ ካለው ጠቅላላ ንብረት በላይ በዕዳ የማይጠየቅ መሆኑ፣
የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት፣
ድርጅቱ ቅርንጫፎች ሊኖሩት የሚችል መሆኑ፣
የተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ስም፣
ድርጅቱ የሚቆይበት ጊዜ።
የሕግ ሰውነትና ኃላፊነት
አንድ ድርጅት የሕግ ሰውነት ይኖረዋል፣ ስለዚህም መብቶችና ግዴታዎች ይኖሩታል።
የአንድ ድርጅት ዕዳዎች ሊሸፈኑ የሚችሉት ድርጅቱ ባለው ጠቅላላ ንብረት ብቻ ይሆናል።
አድራሻ
የአንድ ድርጅት አድራሻ ዋና መሥሪያ ቤት ያለበት ሥፍራ ይሆናል።
ችሎታ
አንድ ድርጅት ዓላማውን ከግቡ ለማድረስና ከዓላማው ጋር የተዛመዱ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስፈልገው ችሎታ ይኖረዋል።
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተው አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ድርጅት፣
በራሱ ስም ለመከሰስና ለመክሰስ፣
የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማግኘት፣ ባለይዞታና ባለቤት ለመሆን፣ ለማስተላለፍና በመያዣነት ለመስጠት፣
ውል ለመዋዋል፣ ብድር ለመበደር፣
የንግድና ሌሎች ተመሳሳይ ሰነዶችን ለማውጣትና ለመቀበል፣
የባንክ ሂሳብ ለመክፈትና ለማንቀሳቀስ፤
ኢንቨስት ለማድረግ፤
ይችላል።
አዲስ
ክፍል 3
የድርጅቱ አቋምና አመራር
አቋም
እያንዳንዱ ድርጅት፣
ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፣
የሥራ አመራር ቦርድ፣
ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ እንደአስፈላጊነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እና
ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ሠራተኞች፤
ይኖሩታል፣
የተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ሥልጣንና ተግባር
ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፣
የዚህ አዋጅ አንቀጽ 12/2/ እንደተጠበቀ ሆኖ የቦርድ አባላትን ይመድባል፣ ያነሳል፣
ከሚመድባቸው አባላት መካከል የቦርዱን ሊቀመንበር ይሾማል፣
ለቦርዱ አባላት ሊከፈል የሚገባውን አበል ይወስናል፣
የውጭ ኦዲተሮችን ይሰይማል፣
የድርጅቱን መነሻ ካፒታል ከመንግሥት ያስመድባል፣
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 21 እና 22 መሠረት የድርጅቱ ካፒታል እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ይወስናል፣
የድርጅቱ የተፈቀደ ካፒታል በአንቀጽ 20/2/ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ እንዲያልቅ የመጠባበቂያ ሂሳቦች እንዲያዙ ወይም ከመንግሥት ገንዘብ እንዲመደብ ያደርጋል፣
ከቦርዱ በሚቀርብለት ሃሳብ መሠረት ከተጣራው ትርፍ ውስጥ በየዓመቱ ለመንግሥት ፈሰስ ሊደረግ የሚገባውን መጠን ይወስናል፣
የድርጅቱን የሂሳብ ሪፖርትና የውጭ ኦዲት ሪፖርት ያጸድቃል፣
በቦርዱ የሚቀርብለትን የድርጅቱን የኢንቨስትመንት ዕቅድ ያጸድቃል፣
አስፈላጊ ሲሆን በቁጥጥሩ ሥር የሚገኝ ድርጅት እንዲፈርስ ከሌላ ድርጅት ጋር እንዲዋሐድ ወይም እንዲከፋፈል ወይም እንዲሸጥ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሃሳብ እያቀረበ ያስወስናል፣
ከቦርዱ ጋር በመመካከር የድርጅቱን ዓመታዊና አጠቃላይ ግቦችን ያጸድቃል፣ አፈጻጸማቸውንም ይከታተላል፣
ለቦርዱ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር እንደጠበቀ ሆኖ፣ የመንግሥት የባለቤትነት መብትን ለማስከበር የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል።
የቦርድ አመሠራረት
የቦርድ አባላት ቁጥር ቢያንስ ሶስት ቢበዛ አሥራ ሁለት ይሆናል።
ከቦርድ አባላት መካከል ቁጥራቸው ከአንድ ሶስተኛ የማይበልጥ የሚሆነው አባላት የሚመረጡት በሠራተኞች ጠቅላላ ጉባዔ ይሆናል። ሌሎች አባላት በተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የሚመደቡ ይሆናል።
የቦርዱ ሊቀመንበር በዚህ አዋጅ አንቀጽ 11/2/ መሠረት ይመደባል፣
የቦርዱ አባላት ምደባና ምርጫ በሙያ፣ በሥራ ልምድና በችሎታ ብቃት ላይ የተመሠረተ ይሆናል፣
ማንኛውም የቦርድ አባል ተወዳዳሪ ያልሆነ የሌላ ድርጅት ቦርድ አባል ሆኖ እንዲሠራም ሊመደብ ይችላል።
የቦርድ አባላት የሥራ ጊዜ ከሶስት /3/ ዓመት ለማያንስ ከአምስት /5/ ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ ይሆናል። አስፈላጊ ሲሆን አንድ የቦርድ አባል የሥራ ጊዜው ሲያልቅ እንደገና ሊመደብ ወይም ሊመረጥ ይችላል።
የቦርዱ የሥራ እንቅስቃሴ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ የአባላቱ የሥራ ዘመን ማብቂያ በአንድ ወቅት አይሆንም።
ማንኛውም የቦርድ አባል የቦርድ አባልነቱን የተወ እንደሆነ ቦርዱ አባልነቱን የተወው አባል በተመደበበት አኳኋን ተተኪ አባል እንዲመደብ ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ማሳሰቢያ ያቀርባሉ።
ለሥራው ተገቢ ላለመሆኑ በቂ ምክንያት ሲኖር አንድን የቦርድ አባል ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በማናቸውም ጊዜ ሊያነሳው ይችላል። ይህ ንዑስ አንቀጽ በሠራተኛው በሚመረጥ የቦርድ አባል ላይም ተፈጻሚ በሚሆንበት ወቅት የሠራተኛው ጠቅላላ ጉባዔ መረጃው እንዲደርሰው ተደርጐ ተተኪ አባል ሊመርጥ ይችላል።
የቦርዱ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት
ቦርዱ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ይሰበሰባል።
አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም ወይም ከቦርዱ አባላት መካከል ቢያንስ ሁለት አባለት ሲጠይቁ በማናቸውም ጊዜ ቦርዱን ሊቀመንበሩ ይሰበስባል።
የቦርዱ ስብሰባ አጀንዳ በቅድሚያ ለቦርዱ አባላት እንዲደርስ ይደረጋል።
ከቦርዱ አባላት መካከል አብዛኛው ከተገኙ ምልዓተ ጉባዔ ይሆናል።
ቦርዱ በድምጽ ብልጫ ይወስናል። ድምጹ እኩል ለእኩል በሚሆንበት ጊዜ ሊቀመንበሩ ወሳኝ ድምጽ ይኖረዋል።
ቦርዱ ከድርጅቱ ሠራተኞች መካከል መርጦ ፀሐፊ ይመድባል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ድምጽ የመስጠት መብት ሳይኖረው በቦርዱ ስብሰባ ላይ ሊገኝ ይችላል።
ቦርዱ በየስብሰባው በተገኙት አባላት የሚፈረም ቃለ-ጉባኤ ይይዛል።
ቦርዱ የራሱን የአሠራር ደንብ ያወጣል።
የቦርዱ ሥልጣንና ተግባር
ቦርዱ፡-
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 11 መሠረት ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን መቅረብ ከሚገባቸው በስተቀር ሌሎች የፖሊሲ ጉዳዮችን ይወስናል።
የድርጅቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ይቀጥራል፣ ደመወዝና አበሉን ይወስናል፣ ያሰናብታል፣
ለድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ የሆኑ የሥራ ኃላፊዎችን ቅጥር ምደባና ስንብት ደመወዝና አበል ያጸድቃል፣
የድርጅቱን የሥራ ፕሮግራም፣ በጀትና የውስጥ ደንብ ያጸድቃል፣ አፈጻጸማቸውንም ይከታተላል፣
የድርጅቱን የረጅም ጊዜ ብድሮችና ክሬዲቶች ያጸድቃል፣
በድርጅቱ ሕልውና ላይ ወሳኝነት የሌላቸውን ቋሚ ንብረቶች ሽያጭ ያጸድቃል፣
የድርጅቱ ሂሣቦችና ንብረቶች ባግባቡ መያዛቸውን ያረጋግጣል፣
ለድርጅቱ ኦዲተሮች የድርጅቱን የሂሳብ መዝገቦች ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ደግሞ ስለድርጅቱ የሥራ አፈጻጸም ወቅታዊ ሪፖርትና የሂሳብ መግለጫዎች ያቀርባል፣
የድርጅቱ ካፒታል እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ሐሳብ ያቀርባል፣
የቦርድ አባላት ተጠያቂነት
የቦርድ አባላት በዚህ አዋጅ መሠረት የተሰጣቸውን ተግባር በጥንቃቄ መፈጸም አለባቸው።
አባላቱ ተግባራቸውን በአግባብ ባለመፈጸማቸው ምክንያት በድርጅቱ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት በአንድነትና በነጠላ ተጠያቂ ይሆናሉ።
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 የተገለጸው ቢኖርም የቦርዱ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ውሳኔው ትክክል አይደለም ብሎ በድምጽ የተለየ የቦርድ አባል ውሳኔው ለሚያስከትለው ጉዳት ተጠያቂ አይሆንም።
የድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሥልጣንና ተግባር
ዋናው ሥራ አስኪያጅ፣
የድርጅቱን ሥራ ያደራጃል፣ ይመራል፣ ያስተዳድራል፣ ይቆጣጠራል፣
ድርጅቱ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት፣ ድርጅቱ በሚያቀርባቸው ክሶችና በድርጅቱ ላይ በሚቀርቡ ክሶች ድርጅቱን ወክሎ ይሠራል፣
ቦርዱን እያሰፈቀደ ለእሱ ተጠሪ የሆነ የሥራ ኃላፊዎችን ይቀጥራል፣ ይመድባል፣ ተግባራቸውን ይወስናል፣
በድርጅቱ የውስጥ ደንብና አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ሌሎች ሠራተኞችን ይቀጥራል፣ ይመድባል፣ ያሰናብታል፣ ደመወዛቸውንና አባላቸውን ይወስናል፣
የድርጅቱን ሂሳቦች ባግባቡ ይይዛል፣ ለድርጅቱ የባንክ ሂሳብ ይከፍታል፣ ያንቀሳቅሳል፣
ለድርጅቱ ሥራ ማስኬጃ የሚውል የአጭር ጊዜ ብድር ውል ይዋዋላል፣ ቦርዱን በማስፈቀድ የረጅም ጊዜ ብድር ይበደራል፣ ለእነዚሁ ዓላማዎች ቦርዱን እያስፈቀደ የድርጅቱን የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት በመያዣነት ይሰጣል፣
የድርጅቱን የሥራ ፕሮግራምና በጀት እንዲሁም የውስጥ ደንብ አዘጋጅቶ ለቦርዱ ያቀርባል፣ ሲፈቀድም ሥራ ላይ ያውላል፣
ቦርዱን በማስፈቀድ በድርጅቱ ሕልውና ላይ ወሳኝነት የሌላቸውን የድርጅቱን ቋሚ ንብረቶች ይሸጣል፣
የቦርዱን ውሳኔዎች ይፈጽማል፣ ያስፈጽማል፣
ቦርዱ በሚወስነው ሁኔታ ለቦርዱ ሪፖርት ያቀርባል፣
አስፈላጊ ሆኖ በተገኘው መጠን ሥልጣኑን ለድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በውክልና ይሰጣል፣
በሥራው ሂደት ላይ የሚመክርና በሥራ ግምገማዎች፣ በዕቅዶችና ውሳኔዎች ላይ የሚወያይ የማኔጅመንት ኮሚቴ ያቋቁማል፣ ስብሰባውንም ይመራል፣
ቦርዱ የሚሰጠውን ሌላ ተግባር ይፈጽማል፣
ዋናው ሥራ አስኪያጅ ለቦርዱ ተጠሪ ይሆናል።
የዋናው ሥራ አስኪያጅ ኃላፊነትና ተጠያቂነት
ዋናው ሥራ አስኪያጅ ተግባሩን በሚፈጽምበት ጊዜ በቸልተኝነት ወይንም ሆን ብሎ በድርጅቱ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት በሕግ ተጠያቂ ይሆናል።
ውክልና
ማናቸውም ድርጅት በዋናው ሥራ አስኪያጅና በዚህ አዋጅ መሠረት ሥልጣን በተሰጣቸው ሌሎች ወኪሎች አማካይነት ሥራውን ይፈጽማል፣ መብት ያገኛል ግዴታ ይገባል።
ክፍል 4
የድርጅቱ ካፒታል
ድርጅት ለማቋቋም ስለሚያስፈልገው ካፒታል
ማናቸውም ድርጅት ካፒታል ይኖረዋል፣
አንድ ድርጅት ለማቋቋም የሚያስፈልገውን መነሻ ካፒታል ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በመንግሥት እንዲመደብለት ያደርጋል። ካፒታሉ በዓይነት ወይም በጥሬ ገንዘብ ሊሆን ይችላል፣ በዓይነት ከሆነ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 መሠረት የተገመተ ወይም በመዝገቡ መሠረት ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል።
ስለተከፈለና ስለተፈቀደ ካፒታል
ማናቸውም ድርጅት ሲቋቋም ድርጅቱ የሚኖረው የተከፈለ ካፒታል መጠን ከተፈቀደው ካፒታል 25 በመቶ ሊያንስ አይችልም።
የአንድ ድርጅት የተፈቀደ ካፒታል ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአምስት ዓመት ውስጥ በሙሉ ተከፍሎ ያልቃል።
የተፈቀደው ካፒታል በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 በተወሰነው ጊዜ በሙሉ ተከፍሎ ካላለቀ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የሦስተኛ ወገኖች መብት ሳይነካ የድርጅቱን ካፒትል ወደ ተከፈለው የካፒታል መጠን ዝቅ ያደርገዋል።
የተፈቀደ ካፒታል ስለመጨመር
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ከመንግሥት ገንዘብ በማስመደብ ወይም ከድርጅቱ ገቢ የድርጅቱ ካፒታል እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል።
ካፒታል ስለመቀነስ
የሦስተኛ ወገኖች መብት ሳይነካ የአንድ ድርጅት ካፒታል የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ሊቀንስ ይችላል፣
የድርጅቱ ካፒታል እንዲቀነስ ኦዲተሮች ሐሳብ ሲያቀርቡ፣
በድርጅቱ ቦርድ በሚቀርበው ሐሳብ መሠረት ካፒታሉ እንዲቀነስ ሲወሰን፣
የድርጅቱ የተፈቀደ ካፒታል በዚህ አዋጅ አንቀጽ 2ዐ ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት በሙሉ ተከፍሎ ያላለቀ ሲሆን።
ክፍል 5
የድርጅት ስምና የንግድ ምልክት
የድርጅት ስም
የአንድ ድርጅት ስም ሥራውን የሚያከናውንበት ስም ሲሆን የድርጅቱን ሥራ በግልጽ የሚያመለክት ይሆናል።
የአንድ ድርጅት ስም የመንግሥት ፖሊሲን እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባርን የሚቃረንና የሶስተኛ ወገኖችን መብት የሚነካ አይሆንም፣
የማናቸውም ድርጅት ስም በሥራ ቦታው በግልጽ እንዲታይ ይደረጋል።
የስም አጠቃቀም ሁኔታዎች
የአንድ ድርጅት ስም አመራረጥ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 23/2/ በተመለከተው መሠረት መሆኑን ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ያረጋግጣል።
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 23/2/ የተመለከተውን የተላለፈ ድርጅት ለደረሰው ጉዳት ካሣ እንዲከፍል እና ወይም ክርክር ባስነሳው ስም እንዳይጠቀም በፍርድ ቤት ሊወሰን ይችላል።
የንግድ ምልክት
የንግድ ምልክት አንድ ድርጅት ለሚያመርተው ዕቃ ወይም ለሚሰጠው አገልግሎት መለያ በማድረግ የሚጠቀምበት ስም፣ ስያሜ፣ ዓርማ፣ ወይም ሌላ ማናቸውም መለያ ምልክት ነው።
የንግድ ምልክት አጠቃቀም ሁኔታዎች
አንድ ድርጅት ማንኛውንም የንግድ ምልክት ሊመርጥ ይችላል።
ማናቸውም የንግድ ምልክት የመንግሥት ፖሊሲ እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባርን የሚቃረንና የሶስተኛ ወገኖችን መብት የሚነካ አይሆንም።
የማናቸውም ድርጅት የንግድ ምልክት በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት አግባብ ባለው መሥሪያ ቤት ይመዘገባል፣ በሰፊው በሚሰራጭ ጋዜጣም ታትሞ ይወጣል።
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 የተመለከተውን የተላለፈ ድርጅት ላደረሰው ጉዳት ካሣ እንዲከፍል እና ወይም ክርክር ባስነሳው የንግድ ምልክት እንዳይጠቀም በፍርድ ቤት ሊወሰን ይችላል።
ክፍል 6
ስለድርጅት ሂሳብና የሂሳብ ምርመራ
ምዕራፍ አንድ
የድርጅት ሂሳብ
የሂሳብ አያያዝ ሥርዓት
ማናቸውም ድርጅት በንግድ አሠራር ተቀባይነት ያለው የሂሳብ አያያዝ ሥርዓት ይኖረዋል። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል።
የሂሳብ ዓመት ሂሣብ መዝጋትና ዓመታዊ ሪፖርት
የአንድ ድርጅት የሂሳብ ዓመት በተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ይወሰናል፣
ማናቸውም ድርጅት ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ሂሣቡን ይዘጋል። ዓመታዊው ሂሳብ የበጀት ዓመቱ ባለቀ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ መዝጋት አለበት።
ድርጅቱ ስላለፈው ዓመት የድርጅቱ ሥራዎችና አቋሞች ሁኔታ፣ ስለተከናወኑ ተግባሮችና በቅርብ ሥራ ላይ ሊውሉ ስለታሰቡ ዋና ዋና ዕቅዶችና ፕሮግራሞች ጭምር ሪፖርት ያዘጋጃል።
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /2/ መሠረት የድርጅቱን ሂሳብ በወቅቱ አለመዝጋት በኃላፊነት የሚያስጠይቅ ይሆናል።
ስለመጠባበቂያ ሂሣቦችና አጠቃቀም
ማናቸውም ድርጅት ሕጋዊ መጠባበቂያ ሂሳብ ይይዛል።
በሌላ ሕግ በተለየ ሁኔታ የተወሰነው እንደተጠበቀ ሆኖ ማናቸውም ድርጅት ከተጣራ ትርፉ ላይ 5 በመቶ በየዓመቱ እያነሳ ሕጋዊ መጠባበቂያው ሂሳብ የድርጅቱን ካፒታል 20 ከመቶ እስኪያህል ድረስ ወደ መጠባበቂያ ሂሣቡ ያስገባል።
ሕጋዊ መጠባበቂያ ሂሣቡ፣
ኪሣራን ለመሸፈን፣
ያልታሰቡ ወጪዎችንና ዕዳዎችን ለመሸፈን፤ ሊውል ይችላል፣
የማናቸውም ድርጅት ቦርድ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑን እያስፈቀደ ሌሎች መጠባበቂያ ሂሣቦችን እንዲያዙ ለማድረግና አጠቃቀማቸውንም ለመወሰን ይችላል።
ስለግብር እና ቀረጥ ክፍያ
የግብር እና ቀረጥ ክፍያን በሚመለከት አግባብ ያላቸው ሕጐች በድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ።
ድርጅቶች በሌላ ሕግ መሠረት ከግብር እና ቀረጥ ነፃ ለመሆን ያላቸውን መብትና ሌላም መብት ይህ አዋጅ አያስቀርባቸውም።
የመንግሥት የትርፍ ድርሻ ክፍያ
የዚህ አዋጅ አንቀጽ 11/8/ እንደተጠበቀ ሆኖ ማናቸውም ድርጅት የሂሣብ ዓመቱ ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ሰባት/7/ ወራት ውስጥ የመንግሥቱን የትርፍ ድርሻ ለመንግሥት ፈሰስ ያደርጋል።
ምዕራፍ ሁለት
ስለ ሂሣብ ምርመራ
የኦዲተሮች አመዳደብ
በሌላ ሕግ ለዋናው ኦዲተር የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የማናቸውም ድርጅት ሂሣብ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በሚሰይማቸው የውጭ ኦዲተሮች ይመረመራል።
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የሚሰይማቸውን የውጭ ኦዲተሮች በዋናው ኦዲተር የወጡ መመዘኛዎችን የሚያሟሉና ከማናቸውም ዓይነት ተጽእኖ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት።
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የውጭ ኦዲተሮችን የሥራ ጊዜ ይወስናል።
ሂሣብ የማስመርመር ግዴታ
የተመርማሪውን ድርጅት ገንዘብ ወይም ንብረት የተረከበ ወጪ ያደረገ የከፈለ ወይም ለሂሳቡ ኃላፊ የሆነ ማንኛውም ሰው ሲጠየቅ ሂሣቡን የማስመርመርና አስፈላጊውን መረጃ የማቅረብ ግዴት አበለት።
የኦዲተሮች ሥልጣን ተግባርና ተጠያቂነት
የንግድ ሕግ ቁጥር 373፣ 374፣ 375፣ 376፣ 378 እና 380 አስፈላጊው ለውጥ ተደርጐባቸው የኦዲተሮችን ሥልጣን ተግባርና ኃላፊነት በሚመለከት ተፈጻሚ ይሆናሉ።
ክፍል 7
ስለመዋሐድና ስለመከፋፈል
መሠረቱ
ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆነ ድርጅቶች አንዱ ሌላውን በመጠቅለልም ሆነ አንድ ሌላ አዲስ ድርጅት በመፍጠር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ሊዋሐዱ ይችላሉ።
አንድ ድርጅት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ አዲስ ድርጅቶች እንዲሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ሊከፋፈል ይችላል።
የማዋሐዱም ሆነ የመከፋፈሉ ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆነው በዚህ አዋጅ መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ ነው።
የወል ድንጋጌዎች
ከአበዳሪ ድርጅት ጋር የብድር ስምምነት አድርጐ ዕዳውን ገና ያልከፈለ ድርጅት ከመዋሐዱ ወይም ከመከፋፈሉ በፊት የአበዳሪውንና የዋስትና ሰጪውን ስምምነት ይጠይቃል።
አንድ ለማዋሐድ ወይም ለመከፋፈል የታሰበ ድርጅት ዕዳ ያለበት ሲሆን በመዋሐድ ወይም በመከፋፈል የሚፈጠረው ድርጅት በገንዘብ ጠያቄዎች በኩል የሚፈለግበትን ግዴታ ለመፈጸም የማይችል ከሆነ የማዋሐዱም ሆነ የመከፋፈሉ ውሳኔ አይሰጥም።
የሚዋሐደው ወይም የሚከፋፈለው ድርጅት ካለፈው የሂሣብ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ መዋሐዱ ወይም መከፋፈሉ እስከተፈጸመበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሂሣብ ይዘጋል፣ በኦዲተርም ይመረመራል።
የመብትና ግዴታ መተላለፍ
በመዋሐዱ ምክንያት ሕልውናውን የሚያጣው ድርጅት መብትና ግዴታ ወደሚጠቀልለው ወይም በመዋሐድ ወደሚፈጠረው አዲስ ድርጅት ይዛወራል።
የሚከፋፈል ድርጅት መብትና ግዴታ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 38 በተመለከተው የመብትና ግዴታ ምደባ መሠረት በመከፋፈሉ ወደሚፈጠሩት አዲስ ድርጅቶች ይዛወራል።
የሚከፋፈል ድርጅት መብትና ግዴታ አመዳደብ
ሀ/ በመከፋፈል ላይ ያለ ድርጅት መብትና ግዴታ በመከፋፈል ወደሚፈጠሩት ድርጅቶች የሚመደበው ጉዳዩ የሚመለከተው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በሚወስነው መሠረት ይሆናል።
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የድርጅቱን መከፋፈል ውሳኔ የያዘና መብትና ግዴታው በመከፋፈሉ በተፈጠሩት ድርጅቶት መካከል እንዴት እንደተመደበ የሚያሳይ የተሟላ ሪፖርት ያዘጋጃል።
የሪፖርቱ አንድ ቅጅ በመከፋፈሉ የተፈጠረው እያንዳንዱ ድርጅት በሚቋቋምበት ጊዜ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል፣ በመከፋፈሉ የተፈጠረው እያንዳንዱ ድርጅትም አንድ ቅጅ ይሰጠዋል።
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የሪፖርቱን ዋና ዋና ነጥቦች የያዘ ማስታወቂያ በሰፊው በሚሰራጩ ጋዜጦች በአማርኛና በእንግሊዝኛ ታትሞ እንዲወጣ ያደርጋል።
በሌላ ሕግ የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ሥራ ድርጅት መከፋፈልን በሚመለከት በዚህ ንዑስ አንቀጽ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ማለት በዚያው ሕግ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የነበረው አካል ነው።
የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ቢኖርም፣ በመከፋፈሉ የተፈጠሩት ድርጅቶች ሁሉ የተከፋፈለው ድርጅት ለሶስተኛ ወገኖች የገባውን ግዴታ በሚመለከት በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት አለባቸው።
ክፍል 8
ስለድርጅቶች መፍረስና ሂሣብ ስለማጣራት
ድርጅት የሚፈርስባቸው ምክንያቶች
ማናቸውም ድርጅት ከሚከተሉት ምክንያቶች ባንዱ ሊፈርስ ይችላል።
በማቋቋሚያው ደንብ የተመለከተው የድርጅቱ የመቆያ ጊዜ ሲያልቅ፣
ድርጅቱ የተቋቋመበት ሥራ ሲያልቅ፣
ድርጅቱ የተቋቋመበት ዓላማ ሲከሽፍ ወይም ሊፈጸም የማይችል ሲሆን፣
ከመቶ ሰባ አምስት (75 በመቶ) የሚሆነው የተከፈለው የድርጅቱ ካፒታል ሲጠፋ፣
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የድርጅቱን ሕልውና የሚነካ ውሳኔ ሲሰጥ፣
የድርጅቱ መክሰር በፍርድ ቤት ሲወሰን።
በኪሣራ ጊዜ ስለሚደረግ የሂሣብ ማጣራት
የመክሰር ሥርዓትን በሚመለከት የንግድ ሕግ 5ኛ መጽሐፍ ድንጋጌዎች አስፈላጊው ለውጥ ተደርጐባቸው በድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ።
በንግድ ሕግ ቁጥር 1166 /1-2/ የተደነገገው ቢኖርም ፍርድ ቤቱ የድርጅት መክሰር በንግድ ሕግ መሠረት በአጭር ሥነ ሥርዓት እንዲመራ ሊወስን ይችላል።
ስለሂሣብ አጣሪዎች ሹመት ተግባርና ሥልጣን
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 39 /1-5/ የተመለከቱት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በዋናው ኦዲተር የወጣውን መመዘኛ የሚያሟላ የድርጅቱ ሠራተኛ ያልሆነ አንድ ወይም ከአንድ በላይ ሂሣብ አጣሪዎች ይሾማል። በቂ ምክንያት ሲያጋጥም ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ሂሣብ አጣሪዎቹን ይሽርና በምትካቸው ሌሎች ሊሾም ይችላል።
የሂሣብ አጣሪዎች በመፍረስ ላይ ያለውን ድርጅት መዝገቦችና ሂሣቦች ይረከባሉ።
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በተለየ ሁኔታ ካልወሰነ በስተቀር፣ ሂሣብ አጣሪዎች የድርጅቱን ንብረት በኃላፊነት ይይዛሉ፣ በዚህ አዋጅ ለቦርዱና ለዋናው ሥራ አስኪያጅ የተሰጠውም ሥልጣንና ኃላፊነት ይኖራቸዋል፣ ሆኖም ግዴታቸው ያላለቀ ውሎችን ለመፈጸም ወይም የሂሣብ ማጣራቱን ተግባር ለማሳካት አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በስተቀር አዲስ ሥራ መጀመር አይችሉም።
ቦርዱ ካለፈው የሂሣብ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የሂሣብ ማጣራት ተግባር እስከተጀመረበት ቀን ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ስለድርጅቱ አቋም ሪፖርት አዘጋጅቶ ለሂሣብ አጣሪዎች ይሰጣል።
ሂሣብ አጣሪዎችና ቦርዱ የድርጅቱን መብቶችና ግዴታዎች ባጭሩ የያዘ መግለጫ በጋራ አዘጋጅተው ይፈርሙበታል።
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በተለየ ሁኔታ ካልወሰነ በስተቀር ቦርዱና ዋናው ሥራ አስኪያጅ ሂሣብ አጣሪዎቹን በሥራቸው ይረዷቸዋል።
ባለገንዘቦችን ስለመጥራት
ሂሣብ አጣሪዎች ድርጅቱ የሚፈርስ መሆኑንና ያላቸውን የገንዘብ ጥያቄም በማስረጃ በማስደገፍ እንዲያቀርብ ለባለገንዘቦች ያስታውቃሉ።
ስማቸው በድርጅቱ መዝገብ ተይዞ ለሚገኘው፣ እንዲሁም በሌላ ሁኔታ ለታወቁ ባለገንዘቦች ማስታወቂያ በሪኮማንዴ ይላክላቸዋል። ሌሎች ባለገንዘቦች በሰፊው በሚሰራጭ ጋዜጣ በየሳምንቱ በሚወጡ ሶስት ተከታታይ ማስታወቂያዎች እንዲያውቁ ይደረጋል። ባለገንዘቦች ያላቸውን የገንዘብ ጥያቄ እንደነገሩ ሁኔታ ደብዳቤ ከደረሳቸው ወይም የመጨረሻው የጋዜጣ ማስታወቂየ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በዘጠና /90/ ቀን ውስጥ የገንዘብ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡
ሂሣብ አጣሪዎች ስለድርጅቱ የሂሣብ አቋም መግለጫ አዘጋጅተው ስለዕዳው አከፋፈል ያላቸውን ሐሳብ የባለገንዘቦችን ዝርዝርና የአከፋፈሉን ቅደም ተከተል /የሚኖር ከሆነ/ በመጨረሻ ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ያቀርባሉ።
ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ሂሣብ አጣሪዎች ያዘጋጁትን የሂሣብ አቋም መግለጫ መሠረት በማድረግና ስለዕዳው አከፋፈል ያቀረቡትን ሃሳብ በማመዛዘን፣
የገንዘብ ጥያቄያቸውን በማስረጃ በማስደገፍ ላቀረቡ ባለገንዘቦች ክፍያው እንዲፈጸም ይፈቅዳል፣
የድርጅቱ ጥሬ ገንዘብ ለባለገንዘቦች መከፈል ያለበት ዕዳ የማይሸፍን ሆኖ ሲገኝ የሶስተኛ ወገኖች መብት ሳይነካ በሚያጸድቀው የሽያጭ ዘዴ አማካይነት የድርጅቱን ንብረቶች ሂሣብ አጣሪዎች እንዲሸጡ ይፈቅዳል።
የድርጅቱ ጠቅላላ ንብረት ዕዳውን ለመክፈል በቂ በማይሆንበት ጊዜና የተፈቀደው ካፒታል በሙሉ ሳይከፈል ከቀረ ሂሣብ አጣሪዎች ቀሪው ሂሳብ እንዲከፈል ተቆጣጣሪውን ባለሥልጣን ይጠይቃሉ።
የባለገንዘቦችን መብት ስለመጠበቅ
የታወቁ ባለገንዘቦች በዚህ አዋጅ አንቀጽ 42/2/ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ውስጥ ጥያቄያቸውን ሳያቀርቡ የቀሩ እንደሆነ ሊከፈላቸው የሚገባ ገንዘብ በባለገንዘቦቹ ስም በባንክ ተቀማጭ ይሆናል።
ባልተጠናቀቁ የድርጅቱ ሥራዎች መነሻነት የሚቀርቡ የገንዘብ ጥያቄዎችን ለመሸፈን የሚያስፈልገው ገንዘብ እንዲሁም ባለገንዘቦቹ ዋስትና ያልተሰጣቸው ከሆነ ክርክር ያስነሱ ዕቃዎችን ለመሸፈን የሚያስፈልገው ገንዘብ ክርክሩ እስከሚወሰን ድረስ ለብቻ ተቀማጭ ሆኖ ይያዛል።
በአንቀጽ 44/2/ መሠረት የድርጅቱ ሕልውና ካበቃ በኋላ የሚቀርብ በድርጅቱ መዝገብ ያልታወቀ ገንዘብ ጠያቂዎች የገንዘብ ጥያቄያቸውን በአንቀጽ 42/2/ በተወሰነው ጊዜ ያላቀረቡት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሆነ፣ በትርፍነት ለመንግሥት ከገባው ኃብት ላይ እንዲከፈላቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። እንዲሁም በሂሣብ አጣሪዎች ቸልተኝነት ምክንያት ያልተከፈላቸው ባለገንዘቦች ሂሣብ አጣሪዎችን በኃላፊነት ሊጠይቁ ይችላሉ።
የመጨረሻ የኃብትና ዕዳ መግለጫ እና የመፍረስ ማስታወቂያ ስለማውጣት
ባለገንዘቦች ከተከፈላቸውና ሊቀርቡ የሚችሉ የገንዘብ ጥያቄዎችን ለመሸፈን የሚያስፈልገው ገንዘብ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 43/1-2/ መሠረት ተቀማጭ ከሆነ በኋላ ሂሣብ አጣሪዎች ድርጅቱ ትርፍ ኃብት ካለው ይህንኑ የሚያሳይ የመጨረሻ የኃብትና የዕዳ መግለጫ አዘጋጅተው ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ያቀርባሉ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለዋናው ኦዲተርም ግልባጭ ያደርጋሉ። ዋናው ኦዲተር የሚሰጠው አስተያየት ካለው ወዲያውኑ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ይሰጣል። ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የገንዘብ ሚንስቴርን ስምምነት በማግኘት የመጨረሻውን የኃብትና የዕዳ መግለጫ ሲያጸድቀው ወዲያውኑ ድርጅቱ እንዲፈርስ መወሰኑን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያስታውቃል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ድርጅቱ የተቋቋመበትን ደንብ ይሠርዛል። ከዚህም ጊዜ ጀምሮ የድርጅቱ ሕልውና ያበቃል።
የፈረሰ ድርጅት መዝገቦች በተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ዘንድ ተቀምጠው ለ10 ዓመት ይቆያሉ። እነዚህን መዝገቦች ለማየት የሚፈልጉ ሰዎችም ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ በመክፈል መመርመር ይችላሉ።
ለመንግሥት ገቢ ስለሚሆን ኃብት
ፈርሶ ሂሣቡ የተጣራ ድርጅት ትርፍ ኃብት ለመንግሥት ገቢ ይሆናል። 

WordPress 



WordPress

WELCOME TO MUHAJER SEMAN SURAFEL WEBSITES HOME ON WORDPRESS

This blog is for individuals and private organizations who want to read the FDRE Constitution as well as the interpretations of the Constitution as well as various laws of our country, various proclamations, government-approved directives, teachings and publications. Laws and the Constitution of our country. It is a website where we volunteer to help the public learn about draft laws and interpretations of the constitution

BLOG CATEGORIE'S

ABOUT CONTACT & MAPS

Share This It!