SUBSCRIBE

Search This Blog

Oct 14, 2020

የሙስና ወንጀል

የሙስና ወንጀል ትርጉምን፣ የክስ ሂደትና የማስረጃ ድንጋጌዎችን ከወንጀል ህጉ ጋር በተጣጣመ መልኩ ማሻሻልና መደንገግ በማስፈለጉ፣

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎች በዋስትና ስለሚለቀቁበት ሁኔታ ዝርዝር ድንጋጌ መደንገግ በማስፈለጉ፣

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ንብረት ስለማገድ፣ ስለማስተዳደርና ስለመውረስ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ማሻሻል በማስፈለጉ፣
የጸረ ሙስና ልዩ ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ድንጋጌዎችን ከሌሎች ህጎች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ማስተካከልና ማሻሻል በማስፈለጉ፣

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀጽ 55(1) መሰረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ
አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ አዋጅ ቁጥር 434/1997” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።
ትርጓሜ

የሙስና ወንጀል ማለት በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች ናቸው፡፡

“የሙስና ወንጀል” ማለት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 የተሰጠው ትርጓሜ ይኖረዋል፡፡

“በሙስና ወንጀል የተገኘ ንብረት” ማለት በተከሳሽ ባለቤትነት ወይም ይዞታ ስር የሚገኝ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሙስና በወንጀል የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ሲሆን ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር ከተከሳሹ በስጦታ የተሰጠ በአደራ የተቀመጠ እና የተሸሸገ፣ ማናቸውም በወንጀል የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ይጨምራል።

“አግባብ ያለው አካልን” ማለት የሙስና ወንጀልን ለመመርመር እና/ወይም ለመክሰስ ሥልጣን የተሰጠው አካል ነው።

“የእግድ ትእዛዝ” ማለት ተከሳሽ በንብረቱ ላይ ያለውን መብት እንዳይጠቀምበት የሚከለክል ትእዛዝ ሲሆን በማናቸውም መንገድ ለሌላ ሰው ማስተላለፍን የመጠቀም መብት መስጠትንና ማስወገድን ይጨምራል።

“አዋጅ“ ማለት የተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/1997 ነው፡፡ ⓘ

“ኮሚሽነር” ማለት የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ነው፡፡ ⓘ

“ጠቋሚ” ማለት ተፈፅሟል ወይም ሲፈፀም ነው ብሎ ያመነውን የሙስና ወንጀል የሚመለከት መረጃ አግባብ ላለው አካል ወይም ለሌላ የፍትህ አካል፣ ለመንግስት መሥሪያ ቤት፣ ለመንግስት የልማት ድርጅት ወይም ለህዝባዊ ድርጅት የበላይ ኃላፊ ወይም ወይም በመመሪያ የሙስና ወንጀል ጥቆማን እንዲቀበል ኃላፊነት ለተስጠው ሌላ አካል የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ሲሆን፣ ለእነዚህ ለተጠቀሱት አካላት ጥቆማ ባያቀርብም የሙስና ወንጀል የተፈፀመበትን ጉዳይ ኦዲት የሚያደርግ ወይም በአዲት ተግባሩ ሙስና መፈፀሙን ያጋለጠ ኦዲተርን እና ጥቆማን የሚያጣራ ወይም የሚመረምር ሰውን ያካትታል፡፡ ⓘ

“የበላይ ኃላፊ” ማለት አንድን የመንግስት መሥሪያ ቤት፣ የመንግስት የልማት ድርጅት ወይም የህዝባዊ ድርጅት በኃላፊነት የሚመራ ሰውን ወይም ምክትሎቹን ወይም ሚኒስትር ዴኤታዎችን ይመለከታል፡፡ ⓘ

“ህዝባዊ ድርጅት” ማለት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 የተሰጠውን ትርጓሜ ይኖረል፡፡ ⓘ

“ሰው” ማለት ማናቸውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው።

የአዋጁ ተፈጻሚነት ወሰን

ይህ አዋጅ በፌዴራልና በክልል ሥልጣን ስር በሚወድቁ የሙስና ወንጀሎች የምርመራና የክስ ሂደት ተፈጻሚ ይሆናል።

ክፍል ሁለት

ስለ ዋስትና የፍርድ ቤት ስልጣን

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ስለተያዙ ሰዎች በዋስትና የመፈታት መብት

በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡ ሆኖም የተከሰሰበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መልቀቅ አይቻልም፡፡ ⓘ

በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡ ሆኖም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ፅኑ እሥራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መለቀቅ አይችልም። ከአራት ዓመት በላይ እና ከአስር ዓመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩም እየተደመሩ ከአስር አመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትና ይከለከላል።

በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰውን መርማሪው ከዚህ በታች በተመለከቱት ሁኔታዎች የዋስትና ወረቀት በማስፈረም ወይም መያዣ በማስያዝ ሊለቀው ይችላል፡-

ተፈጸመ የተባለው ወንጀል ለመፈጸሙ የሚያጠራጥር ከሆነ፣ ወይም

የተያዘው ሰው ወንጀሉን ለመፈጸሙ የሚያጠራጥር ከሆነ፣ ወይም

ተፈጸመ የተባለው ወንጀል በጽኑ እስራት የማያስቀጣ ከሆነ

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት በዋስትና ወረቀት ያልተለቀቀ ተከሳሽ በዋስትና ወረቀት እንዲለቀቅ ፍርድ ቤትን ለመጠየቅ ይችላል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተከሳሹ ወይም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት በተጠርጣሪው የሚቀርበውን በዋስትና ወረቀት የመለቀቅ ጥያቄን ፍርድ ቤቱ ከዚህ በታች በተመለከቱት ሁኔታዎች መፍቀድ አይችልም።
ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ በዋስትና ቢለቀቅ ይጠፋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ወይም፣
ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ በዋስትና ቢለቀቅ ማስረጃዎችን ያጠፋል ወይም ሌላ ወንጀል ይፈጽማል ተብሎ ሲገመት፣
የዋስትና መብትን በማክበር ወይም በመከልከል በሚሰጥ ወሳኔ ላይ ስለሚቀርብ ይግባኝ
በዚህ አዋጅ በአንቀጽ 4 በተመለከተው መሰረት ፍርድ ቤት ዋስትናን በሚመለከት በሚሰጠው ትእዛዝ ላይ ይግባኝ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ይግባኙ የቀረበው በዋስትና መለቀቁን ወይም የዋስትና ገንዘብ መጠኑን በመቃወም ከሆነ ጉዳዩ በይግባኝ ታይቶ እስኪወሰን ድረስ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔው ሳይፈጸም ይቆያል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሙስና ወንጀል የተጠረጠረው ወይም የተከሰሰው ሰው በዋስትና እንዲለቀቅ የወሰነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ መጠየቁ የሚያስረዳ የጽሑፍ ማስረጃ ከይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ለማምጣት አግባብ ነው ብሎ በሚወስነው ጊዜ ውስጥ መርማሪው ወይም አቃቤ ህጉ ማስረጃውን ካላመጣ በቀር አስፈላጊው ስነስርዓት ተሟልቶ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ እንዲለቀቅ በውሳኔው ላይ መግለጽ አለበት፡፡
የመንቀሳቀስ መብትን ስለመገደብ
ፍርድ ቤቱ በዚህ አዋጅ በአንቀጽ 4 ወይም 5 በተመለከተው መሰረት የዋስትና መብቱ በተከበረለት ሰው ላይ ከዚህ በታች ከተመለከቱት አንዱን ወይም ከአንድ በላይ ትእዛዞች ሊሰጥ ይችላል፡፡
ከተወሰነ ክልል ውጭ እንዲይንቀሳቀስ፣
ማስረጃ ሊያጠፋ በሚችልባቸው የተወሰኑ ቦታዎች እንዳይደርስ፣
በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ አግባብ ላለው የምርመራ አካል ሪፖርት እንዲያደርግ፣
ወደውጭ አገር እንዳይወጣ
የሙስና ወንጀሎችን የማየት ስልጣን ስላለው ፍርድ ቤት
አግባብ ባለው ህግ መሠረት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን እንዲታዩ የተደነገጉት እንደተጠበቁ ሆነው ሌሎች በፌዴራል መንግሥት ሥር የሚወድቁ የሙስና ወንጀሎችን በሚመለከት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን አለው፣
አግባብ ባለው ሕግ መሠረት በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን እንዲታዩ የተደነገጉት ክሶች እንደተጠበቁ ሆነው ሌሎች በክልል መንግሥት ሥር የሚወድቁ የሙስና ወንጀሎችን በሚመለከት የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን አለው፣
ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ አስተዳደሮች ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን በመጀመሪያ ደረጃ የማየት ሥልጣን እንደ ሁኔታው አግባብ ባለው የፌዴራል ፍርድ ቤት የሚካሄድ ይሆናል፣
ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ የሚነሱ የመያዝ፣ የብርበራ፣ የቀነ ቀጠሮ፣ በማረፊያ ቤት የማቆየት፣ የዋስትና፣ የእግድ እንዲሁም ከምርመራ ጋር የተያያዙ ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች የሚታዩት የሙስና ወንጀሉን ክስ ለማየት ሥልጣን በተሰጠው ፍርድ ቤት ይሆናል፡፡

በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (4) የተደነገገው ቢኖርም፦ ⓘ

እነዚህ የሥነ-ሥርዓት ገዳዮች የሙስና ወንጀሎችን የማየት ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት እንዲታዩ መደረጉ የተከሳሽን መብት የሚያጣብብ ወይም ማስረጃ እንዲጠፋ ምክንያት የሚሆን ወይም ተገቢ ላልሆነ ወጪ የሚዳርግ መሆኑን አግባብ ያለው አካል ካመነበት እንደ ሁኔታው በአቅራቢያው በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታይ ሊወስን ይችላል፤

በዚህ ንዑስ አንቀፅ በፊደል ተራ (ሀ) በተመለከተው አግባብ ጉዳዩ በቀረበለት ፍርድ ቤት በተሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን አግባብነት ወደ አለው ፍርድ ቤት ይገባኝ መጠየቅ ይችላል። ይግባኝ የቀረበለት ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡

ክፍል ሦስት

ስለ እግድ

መርህ ⓘ

የዚህ አዋጅ አንቀጽ 10 እንደተጠበቀ ሆኖ ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል የተገኘ ማናቸውንም ንብረት ለማገድ ይችላል፡፡

መርማሪ ወይም ዐቃቤ ህግ በሙስና ወንጀል የተገኘ ንብረት እንዲታገድ በቃለ መሀላ በተደገፈ መረጃ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡

ለእግድ የሚቀርብ ማመልከቻ የወንጀል ክስ ከተመሰረተ በኋላ ወይም የወንጀል ክሱ ከመመስረቱ በፊት ሊቀርብ ይችላል፡፡

መርህ

የአዋጁ አንቀፅ 10 እንደተጠበቀ ሆኖ ፍርድ ቤት በወንጀል የተገኘ ማንኛውም ንብረት እና በወንጀል የተገኘው ንብረት ያፈራውን ንብረት ለማገድ ይችላል፡፡

መርማሪ ወይም ዐቃቤ ህገ በወንጀል የተገኘ ማንኛውም ንብረት እና በወንጀል የተገኘው ንብረት ያፈራው ንብረት እንዲታገድ በቃለ መሀላ በተደገፈ መረጃ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡

ለእግድ የሚቀርብ ማመልከቻ የወንጀል ክስ ከተመሰረተ በኋላ ወይም የወንጀል ከሱ ከመመስረቱ በፊት ሊቀርብ ይችላል፡፡

በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (1)፣ (2) እና (3) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ አግባብ ያለው አካል የበላይ ኃላፊ በፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እስኪወጣ ድረስ ንብረቱ እንደሚባክን ሲያምንበት ለ48 ስዓት የሚፀና ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ መስጠት ይችላል።

ሌሎች ንብረቶች ስለሚታገዱበት ሁኔታ ⓘ

በሙስና ወንጀል የተገኘ ለመሆኑ መረጃ ባይቀርብም ምርመራ በተጀመረበት ወይም ክስ በቀረበበት የሙስና ወንጀል ተከሳሽ ያገኘው የማይገባ ጥቅም ወይም ያደረሰው ጉዳት ለመኖሩ በቃለ መሀላ ሲረጋገጥ በወንጀሉ ተገኘ ከተባለው የማይገባ ጥቅም ወይም ደረሰ ተብሎ ከሚገመተው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ በተከሳሽ ስም በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ ወይም ንብረት ወይም በተከሳሽ ስም ያለ ንብረት እንዳይሸጥ፣ እንዳይለወጥ፣ እንዳይተላለፍ ታግዶ እንዲቆይ በመርማሪ ወይም በአቃቤ ህግ አቤቱታ ሲቀርብ ፍርድ ቤት የእግድ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት በሚሰጥ የእግድ ትእዛዝ ተጠርጣሪው በታገደው ንብረቱ የመጠቀም መብት አይነካም፡፡

ሌሎች ንብረቶች ስለሚታገዱበት ሁኔታ

በሙስና ወንጀል የተገኘ ለመሆኑ መረጃ ባይቀርብም ምርመራ በተጀመረበት ወይም ክስ በቀረበበት የመኳስና ወንጀል ተከሳሽ ያገኘው የማይገባ ጥቅም ወይም ያደረሰው ጉዳት ለመኖሩ በቃለ መሀላ ሲረጋገጥ በወንጀሉ ተገኘ ከተባለው የማይገባ ጥቅም ወይም ደረስ ተብሎ ከሚገመተው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ በተክሳሽ፣ በትዳር ጓደኛው ወይም ከ 18 ዓመት በታች በሆነ ልጁ ስም በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ ወይም ንብረት ወይም በእነዚሁ ሰዎች ስም ያለ ንብረት እንዳይሸጥ፣ እንዳይለወጥ ወይም እንዳይተላለፍ ታግዶ እንዲቆይ በመርማሪ ወይም በዐቃቤ ህግ አቤቱታ ሲቀርብ ፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል።

በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) መሠረት የሚሰጥ የአንድ ትእዛዝ ተጠርጣሪው በታገደው ንብረቱ የመጠቀም መብቱን አይነካም።

በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (2) የተደነገገው ቢኖርም ተጠርጣሪው በባንክ በተቀመጠው ገንዘብ ወይም ንብረት የመጠቀም መብት አይኖረውም። ሆኖም ሁኔታዎች ሲያስገድዱ ፍርድ ቤቱ እንዲታገድ ከተደረገው ከዚሁ ገንዘብ ወይም ንብረት ውስጥ ተጠርጣሪው ሊጠቀምበት የሚገባ መጠን ወስኖ እንዲጠቀም ሊፈቅድለት ይችላል።

ተጠርጣሪው በተፈቀደለት የመጠቀም መብት ሲጠቀም በንብረቱ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ሲገመት መርማሪው ወይም ዐቃቤ ሕጉ ንብረቱን ከጉዳት ለመከላከል የሚጠቅም ትእዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ በቀረበው ጥያቄ ላይ ተገቢ የሆነውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ስለማይታገዱ ንብረቶች

ለተከሳሹ የእለት ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ንብረቶች በአንቀጽ 8 በተመለከተው መሰረት የእግድ ትእዛዝ አያርፍባቸውም፣ የእግድ ትእዛዝ ከማያርፍባቸው ውስጥ በተለይ የሚከተሉት ይገኙበታል፣

ለተከሳሹና ለቤተሰቡ የዕለት አገልግሎት የሚጠቅሙ ልብሶች፣ የምግብ ማብሰያ የሆኑ የቤት ቁሳቁስ የመኝታ አልጋ፣ የአልጋ ልብሶችና የብርድ ልብሶች፣

ለራሱና ለቤተሰቡ ለዕለት ኑሮ ጠቃሚ የሚሆን ከሶስት ወር ያልበለጠ ስንቅ፣

የተከሳሹንና የቤተሰቡን የእለት ኑሮ ለማሟላት የሚያገለግሉ ቀላል መሳሪያዎች፣

ተከሳሹና ቤተሰቡ የሚተዳደሩበት ሌላ ንብረት የሌላቸው ሲሆንና የሚተዳደሩት ከታገደው ንብረት ከሚገኝ ገቢ ከሆነ መሰረታዊ ፍላጎትን ለማሟላት ለተከሳሹና ለቤተሰቡ ፍርድ ቤቱ በቂ ነው ብሎ የሚገምተውን ያህል ገቢ፣

የማመልከቻው ይዘት

የእግድ ትእዛዝ እንዲሰጥ የሚቀርብ በቃለ መሀላ የተደገፈ ማመልከቻ፣

የወንጀሉን ፍሬ ነገርና በየደረጃው የተወሰዱትን እርምጃዎች፤ ክስ ያልተመሰረተ ከሆነ ጉዳዩ የሚገኝበትን ደረጃ የሚያሳይ መረጃ

የሚታገደው ንብረት ወይም ገንዘብ በሙስና ወንጀል የተገኘ ንብረት መሆኑን የሚያሳዩ ወይም ተፈጽሞአል በተባለውና ምርመራ በተጀመረበት የሙስና ወንጀል አማካይነት ተጠርጣሪው ያገኘው የማይገባ ጥቅም ወይም የደረሰ ጉዳትን በሚመለከት አሳማኝ ምክንያቶች፣

የንብረቶቹን ዝርዝርና አድራሻ፣

የያዘ መሆን ይኖርበታል።

የእገዳው ማመልከቻ እና የእግድ ትእዛዙን በመደገፍ የሚቀርቡ ጉዳዮች በተሟላና ግልጽ በሆነ ሁኔታ በቃለ መሀላው ውስጥ በዝርዝር መገለጽ ይኖርባቸዋል።

የእግድ ትእዛዝ ከተሰጠ በኋላ በተጨማሪ የእግድ ትእዛዝ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ሁኔታ የተፈጠረ እንደሆነ መርማሪው ወይም ዐቃቤ ህጉ ለፍርድ ቤት ተጨማሪ የእግድ ትእዛዝ እንዲሰጥ ማመልከት ይችላል።

የእግድ ትእዛዝ ስለመስጠት

የዚህ አዋጅ አንቀጽ 10 እንደተጠበቀ ሆኖ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ማመልከቻና ሰነዶች ከመረመረ በኋላ የእግዱን አስፈላጊነት ካመነበት የእግድ ትእዛዝ መስጠት ይችላል።

ተከሳሹ በሌለበት የእግድ ትእዛዝ ከተሰጠ መርማሪው ወይም ዐቃቤ ህጉ ትእዛዙንና የቃለ መሀላውን ግልባጮች ለተከሳሹና በትእዛዙ ስሙ ለተጠቀሰው ሌላ ሰው ያደርሳል፣ የእግድ ትእዛዙን ለሚመለከተው ለማናቸውም ሰው ያስታውቃል።

ፍርድ ቤቱ የተለየ ትእዛዝ ካልሰጠ በቀር ተከሳሽ በሌለበት የተሰጠ የእግድ ትእዛዝ የጸና ይሆናል፡፡

ንብረት ጠባቂ ስለመሾም

ፍርድ ቤት የእግድ ትእዛዝ የሰጠበትን ንብረት አጠባበቅ በተመለከተ በዚህ አዋጅ ከአንቀጽ 17 እስከ 21 የተመለከቱት ተፈጸሚ ይሆናሉ።

አግባብ ያለው አካል ኃላፊነት

አግባብ ያለው አካል፡-

ንብረት ጠባቂው ንብረቱን በአግባቡ ማስተዳደሩን ይከታተላል፡፡

ንብረት ጠባቂው ንብረቱን በአግባቡ አላስተዳደረም ብሎ ካመነ ምክንያቱን በመግለጽ መግለጫ ለፍርድ ቤት ያቀርባል።

በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 መሰረት አግባብ ያለው አካል ያቀረበውን መግለጫ ተመልክቶ ፍርድ ቤቱ ተገቢ የመሰለውን ትእዛዝ ይሰጣል፡፡

የእግድ ትዕዛዝ ስለሚቋረጥበት ሁኔታ

ፍርድ ቤቱ የውርስ ውሳኔ የሰጠ ከሆነ የእግድ ትእዛዙ ይቋረጣል።

ተከሳሹ በነጻ የተለቀቀ እንደሆነ የእግድ ትእዛዙ እንዲነሳለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ሊያቀርብ ይችላል።

በዚህ አንቀጽ በንኡስ አንቀጽ 2 በተመለከተው መሰረት ለቀረበው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ አስተያየቱን እንዲሰጥ ይጠይቃል፡፡ አስተያየቱን ካዳመጠ በኋላ በቀረበው አቤቱታ መሰረት እግዱ እንዲነሳ ወይም እግዱ ሳይነሳ እንዲቆይ ሊወስን ይችላል።

የእግድ ትእዛዝ ስለማንሳት ወይም ስለማሻሻል

የእግድ ትእዛዝ የደረሰው ወይም ትእዛዙን እንዲያውቅ የተደረገ ማናቸውም ሰው የእግዱ ትእዛዝ እንዲነሳለት ወይም እንዲሻሻል ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የቀረበውን ማመልከቻና ማስረጃ ፍርድ ቤቱ ከተቀበለው ለመርማሪው ወይም ለአቃቤ ህጉ እንዲደርሰው በማድረግ ምላሽ እንዲሰጥበት ያደርጋል፡፡

የእግድ ትእዛዝ እንዲነሳ ወይም እንዲሻሻል የቀረበው አቤቱታ በበቂ ምክንያት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ሰጥቶ የነበረውን የእግድ ትእዛዝ እንዲሻሻል ወይም እንዲነሳ ሊያደርግ ይችላል።

ከዚህ በላይ በንዑስ አንቀጽ 3 በተመለከተው መሰረት ለመወሰን ተጣርቶ እንዲቀርብለት ፍርድ ቤቱ ባለሙያ ሊመድብ ይችላል። ንዑስ ክፍል ሶሰት ንብረት ጠባቂ ስለመሾም

የንብረት ጠባቂ ስለሚሾምበት ሁኔታ

ፍርድ ቤቱ የሚመችና ትክክለኛ መሆኑን የገመተ እንደሆነ የእግድ ትእዛዝ የተሰጠበትን ንብረት በተመለከተ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱትን ትእዛዞች ለመስጠት ይችላል፣

ንብረቱን ተቀብሎ የሚጠብቅ ሰው መርጦ መሾም፣

ንብረቱን በይዞታ ወይም በአደራ አስቀማጭነት ወይም በጠባቂነት ለሌላ ሰው ሆኖ የያዘን ሰው ንብረቱን እንዲለቅ፣

የተለቀቀውን ንብረት ጠባቂው ተረክቦ በይዞታው ስር እንዲያደርግ እንዲጠብቅና እንዲያስተዳድር ለማዘዝ፣

ተቀባዩ የተረከበውን ንብረት ለመጠበቅ ለማስተዳደርና ለማሻሻል የሚያስችለው ሥልጣን ለመስጠት።

ፍርድ ቤቱ ንብረት ጠባቂው ስለተቀበለው ንብረት የመክሰስ ወይም የመከሰስ መብት እንዲኖረው እንዲሁም ከንብረቱ የሚገኝ ኪራይ ትርፍ ወይም ሌላ ማንኛውም ገቢ ለመሰብሰብና የሰበሰበውንም ገንዘብ ጠቃሚ ለሚሆን ጉዳይ ለማዋል እንዲችል ወይም ፍርድ ቤቱ ተገቢ መስሎ የታየውን ሌላ ስልጣን ሊሰጠው ይችላል።

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 መሰረት ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ትእዛዝ ንብረት ጠባቂውን ለመሾም የሚያስፈልገውን ወጪ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። አስፈላጊ ሆኖ ካገኘውም ሹመቱን ከመስጠቱ በፊት አስፈላጊው ማጣራት እንዲደረግ ማዘዝ ይችላል።

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) መሰረት በንብረት ጠባቂነት የሚሾመው የተፈጥሮ ሰው የሆነ እንደሆነ ይህ ሰው መልካም ሥነ ምግባርና ችሎታ ያለው እንዲሁም ከተከሳሽ ጋር ዝምድና ወይም የጥቅም ግንኙነት የሌለው መሆን ይኖርበታል።

በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1(ሀ) መሰረት በንብረት ጠባቂነት የሚሾመው የህግ ሰውነት ያለው ከሆነ ያለፉት ሶስት አመታት የሂሳብ አያያዙ ንጹህ መሆኑንና የጥቅም ግጭት አለመኖሩ መረጋገጥ ይኖርበታል።

በዚህ አንቀጽ መሰረት ንብረት ጠባቂ የሚሆኑትን ለማሾም በመርማሪው ወይም በአቃቤ ህጉ ወይም በተጠርጣሪው ሊቀርብ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱም እንደሁኔታው የሌላኛውን ተከራካሪ ወገን አስተያየት በመጠየቅ ይወስናል፡፡

ስለንብረት ጠባቂው አበል ክፍያ

ለንብረት ጠባቂው ከተከበረው ንብረት ላይ የሚከፈለውን አበል በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ጠቅላላ ወይም ልዩ ትእዛዝ ይወሰናል፡፡

ንብረት ስለማረካከብ

በዚህ አዋጅ መሰረት የተከበረ ንብረትን ለንብረት ጠባቂው ለማረካከብ የሚወጣው ወጪ ከተከበረው ንብረት ላይ በንብረት ጠባቂው አማካይነት ስለሚከፈልበት ሁኔታ በፍርድ ቤት ይወሰናል፡፡

ስለንብረት ጠባቂው ግዴታዎች

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 17 መሰረት የሚሾም ንብረት ጠባቂ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱት ግዴታዎች ይኖሩታል።

እንዲያስተዳድር የተሾመበትን ንብረት በተመለከተ ኃላፊ ለመሆን የሚችል ዋስ ወይም መያዣ የመስጠት፣

ፍርድ ቤቱ በሚወስነው ጊዜና የአቀራረብ ፎርም መሰረት የሂሳብ መግለጫ እየሰራ የማቅረብ፣

ፍርድ ቤቱ በሚወስነው መሰረት የሚፈለግበትን ገንዘብ የመክፈል እና

በራሱ ከባድ ቸልተኝነት ወይም ሆን ብሎ ባደረገው ጉድለት በተረከበው ንብረት ላይ ላደረሰው ጉዳት ሀላፊ ሆኖ የመክፈል፡፡

የንብረት ጠባቂውን ግዴታ ስለማስከበር

ንብረት ጠባቂው በራሱ ከባድ ቸልተኝነት ወይም ሆን ብሎ በንብረቱ ላይ ጉዳት ወይም ጉድለት ያደረሰ እንደሆነ የሚፈለግበትን ገንዘብ እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ሊያዘው ይችላል፡፡

ገንዘብ እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ካዘዘው በኋላ ሳይፈጽም የቀረ እንደሆነ ጠባቂው ንብረቱ ተሸጦ ከሽያጩ ላይ የተገኘው ሀብት በቸልተኝነት ወይም ሆነ ብሎ ያደረሰው ጉድለት እንዲተካ ወይም ጉዳቱን ለመጠገን የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንዲከፍል በማዘዝ ቀሪ ገንዘቡ እንዲመለስለት ለማድረግ ይችላል፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት ስለማሸግና የሀብት ዝርዝር ስለማዘጋጀት

መርህ

ዕግድ የተሰጠበትን ንብረት አሽጎ መጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በዚህ ክፍል የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ።

በፍርድ ቤት ትእዛዝ የተደረገውን እሽግ ፍርድ ቤቱ እንዲነሳ ካላዘዘ በቀር ማንም ሰው እሽጉን ለመቅደድ ወይም ለመክፈት አይችልም። በጉዳዩ ያገባኛል የሚል ወገን እሽጉ እንዲነሳለት ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡

እሽግ እንዲደረግ ስለሚቀርብ ማመልከቻ

መርማሪው ወይም ዐቃቤ ህጉ ንብረቱን ማሸግ አስፈላጊ መሆኑን በቃለ መሀላ ወይም በሌላ መንገድ በተረጋገጠ ማስረጃ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡

የወንጀሉ ጉዳይ ውሳኔ ከማግኘቱ በፊት ፍርድ ቤት በራሱ አስተያየት ወይም ማመልከቻ ሲቀርብለት የማሸግ ትዕዛዝ ለመስጠት ይቻላል፡፡

ፍርድ ቤት የማሸግ ትዕዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ ይህንን ስራ ለመፈጸም ተገቢ የሆነ ሰው ከዚህ በኋል “አሻጊ” በመባል የሚታወቅ መርጦ ይሾማል፡፡

ስለመዝገብ

አሻጊው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት የእሽጉ ስራ ከተፈጸመ በኋላ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጹትን ጉዳዮች የሚያመለክት የራሱ ፊርማ ያረፈበት እሽጉ የተደረገበት ቀንና ዓመተ ምህረት ያለበት መዝገብ ያዘጋጃል፡፡

የፍርድ ቤቱ ትእዛዝና ትእዛዙ የተሰጠበት ቀንና ዓመተ ምህረት፣

የታሸጉትን ነገሮች ዝርዝርና የሚገኙበትን ሥፍራ፣

እንዲታሸጉ ከታዘዙት ውስጥ መገኘትና መታሸግ የሚገባቸው ሆነው ሳይገኙ የቀሩትን /የጎደሉትን/ ነገሮች ዝርዝር፣

የታሸጉ ነገሮች ያሉበትን ቤት ወይም የሚገኙበትን ቦታ የሚጠብቀውን ወይም ለዚሁ ቤትና ስፍራ አላፊ የሆነ ሰው ካለ ስሙንና አድራሻውን፣

የታሸጉ ንብረቶች የሚገኙበት ቤት ወይም ቦታ ቁልፍ ያለው ሲሆን አሻጊው መክፈቻዎቹን ለፍርድ ቤቱ ሬጂስትራር ማስረከብ አለበት።

ስለማይታሸጉ ነገሮች

ከዚህ ቀጥሎ በተመለከቱት ንብረቶች ላይ የእሽግ ትእዛዝ አያርፍባቸውም

በተፈጥሮአቸው የሚበላሹ ወይም ቶሎ የሚሻግቱና የሚበሰብሱ ሲሆኑ፣

በመታሸጋቸው ምክንያት የሚበላሹ ወይም ቶሎ የሚሻግቱና የሚበሰብሱ ሲሆኑ፣

ለባለንብረቱ አስፈላጊ የሆኑና ፍርድ ቤቱም አስፈላጊ መሆናቸውን ተረድቶ እንዳይታሸግባቸው ያዘዘ ሲሆን፣

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1(ሐ) በተመለከተው መሰረት ፍርድ ቤቱ እንዲይታሸጉ ትእዛዝ የሰጠባቸውን ነገሮች ዝርዝር አሻጊው አዘጋጅቶ ማቅረብ አለበት።

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) መሰረት የእሽግ ትእዛዝ እንዲያርፍበት የተደረገው ንብረት በሐራጅ ተሸጦ ገንዘቡ ተቀማጭ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ ለማዘዝ ይችላል።

ስለኑዛዜዎችና ስለሌሎች የጽሁፍ ሰነዶች

አሻጊው በሚያሽገው ነገር ውስጥ የኑዛዜ ጽሁፎች ወይም ቀድሞ የታሸጉ ነገሮች ወይም ሌሎች ሰነዶች ያገኘ እንደሆነ የነዚህኑ ጽሁፎች ዝርዝር አዘጋጅቶ ባንድ ላይ ጠቅልሎ በእሽጉ ውስጥ እንዲቀመጡ ካደረገ በኋላ ስለዚሁ ጉዳይ ትእዛዝ እንዲሰጥበት ያዘጋጀውን ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ ያቀርባል።

ፍርድ ቤቱም እነዚህ ሰነዶች ስለሚቀመጡበት ሁኔታና ስለአያያዛቸው ተስማሚ መስሎ የታየውን ውሳኔ ይሰጣል።

እሽግን ስለማንሳት

እሽግ እንዲነሳ ማመልከቻ ሲቀርብ ወይም ፍርድ ቤቱ በራሱ አስተያየት እሽጉን ማንሳት ተገቢ መሆኑን ሲገምት ትእዛዙን በሚሰጥበት ጊዜ ለጉዳዩ አግባብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ እንዲቀርቡ ያዛል፣ ባለጉዳዮቹም ቀርበው ያላቸውን ሀሳብ ለመግለጽ ይችላሉ፡፡

እሽጉ እንዲነሳ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ከሰጠ በኋላ አሻጊው እሽጉን በማንሳት እሽጉ ሲከፈት የተገኙትን ነገሮች ዝርዝር አዘጋጅቶ ከፈረመባቸው በኋላ ቀኑንና ዓመተ ምህረቱን ጽፎ ያቀርባል፡፡

የንብረቶችን ዝርዝር ስለማዘጋጀት

ትእዛዝ የተሰጠበትን ንብረት ዝርዝር እንዲዘጋጅና እንዲታወቅ ማስፈለጉን ፍርድ ቤቱ ሲረዳው ይህንኑ ዝርዝር ለማዘጋጀት ይችላል ብሎ የሚገምተውን ሰው/ ከዚህ ቀጥሎ “መዝጋቢ” በመባል የሚታወቅ/ መርጦ የዚህኑ ንብረት ዝርዝር አዘጋጅቶ እንዲቀርብ ትእዛዝ ይሰጣል።

መዝጋቢው ከሁለት የማያንሱ ምስክሮች ባሉበት በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ላይ ተለይቶ የተገለጸውን የንብረት ዝርዝር ያዘጋጃል። ዝርዝሩም ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱትን ነገሮች ይይዛል፡፡

የንብረቱ ዝርዝር እንዲዘጋጅ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትእዛዝ እና

የተመዘገቡትን ንብረቶች ትክክለኛ ዝርዝር ከዋጋቸው ግምት ጋር።

ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ከሰጠ የንብረቶቹ ዋጋ የሚገመተው በፍትሀ ብሄር ሥነሥርአት ሕግ አንቀፅ 131 በተመለከተው መሰረት በልዩ አዋቂ /ኤክስፐርት/ አማካይነት ይሆናል፡፡ ልዩ አዋቂው ባደረገው የዋጋ ግምት ዝርዝር መግለጫ ላይ ቀኑንና ዓመተ ምሕረቱን ጽፎና ፈርሞበት ከመዝጋቢው ራፖር ጋር ይያያዛል።

የመዝጋቢው ራፖር የተጻፈበት ቀንና ዓመተ ምህረት ተሞልቶበትና ተፈርሞበት ለፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ፍርድ ቤቱም በተለይ ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀው መዝገብ ውስጥ በፍርድ ቤቱ ሬጂስትራር እንዲመዘገብ ካደረገ በኋላ ጉዳዩ ከሚመለከተው መዝገብ ጋር በማያያዝ አባሪ ሆኖ እንዲቀመጥ ያደርጋል።

ክፍል አራት

ስለንብረት አወራረስ ሥነሥርአት

በፍርድ ቤት ንብረት እንዲወረስ ስለሚወሰንበት ሁኔታ ⓘ

በሙስና ወንጀል ተከሳሽ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ በሙስና ወንጀሉ የተገኘ ተመጣጣኝ ንብረት እንዲወረስ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ንብረት ስለሚወረስበት ሁኔታ

ተከሳሽ በሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ፡-

በሙስና ወንጀል የተገኘ ለመሆኑ የተረጋገጠ ንብረትና በወንጀሉ ከተገኘው ንብረት ያፈራው ንብረት ወይም በሙስና ወንጀሉ ከተገኘው ጥትምና በወንጀል ከተገኘው ንብረት ያፈራው ንብረት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ማናቸውም የተከሳሹ ንብረት እንዲወረስ፣ ወይም

በወንጀሉ ምክንያት ከራሱ ያገኘው ጥቅም ባይኖርም ሌሎች ሰዎች ጥቅም ማግኘታቸው ወይም በግለሰብ፣ በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ጥቅም የደረሰ ጉዳት መኖሩ ከተረጋጋጠ ሌሎች ሰዎች ካገኙት ጥቅም ወይም ደረሰ ተብሎ ከሚገመተው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የተከሳሽ ንብረት በማካካሻነት እንዲወረስ፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ለዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) አፈፃፀም የተከሳሹ ንብረት በሙስና ከተገኘው ጥቅም ወይም ከደረሰው ጉዳት ያነሰ እንደሆነ ወይም በተከሳሹ ስም የተመዘገበ ንብረት ያልተገኘ እንደሆነ ውሳኔው በተከሳሹ የጋራ ንብረት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል።

ለዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (2) አፈፃፀም የተከሳሹ የጋራ ንብረት በተከሳሹ እና በሌላ ሰው ስም በጋራ የተያዘ ንብረት ወይም በህግ እንደ የጋራ ንብረት የሚወሰድ ንብረት ሲሆን በተከሳሹ የትዳር ጓደኛ ወይም ከ18 ዓመት በታች ዕድሜ ባለው ልጁ ወይም በእነዚህ በሁለቱ ስም በጋራ ያለ ንብረት የተከሳሹ የጋራ ንብረት እንደሆነ ይገመታል። ሆኖም የሚመለከተው ሰው ንብረቱ ከተከሳሹ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የግል ሀብቱ መሆኑን በግልፅ የሚያስረዳ ማስረጃ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ይህን ግምት ማፍረስ ይችላል።

የመውረስ ውሳኔን ስለማዘግየት

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በወንጀል ድርጊቱ ጥቅም ማግኘት አለማግኘቱን ወይም ተመላሽ የሚሆነውን የንብረት መጠን ለመወሰን ተጨማሪ ማስረጃዎች ማግኘት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው የጥፋተኝነት ውሳኔ ከሰጠበት ቀን አንስቶ ከስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ውሳኔውን ሊያዘገየው ይችላል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የመውረስን ውሳኔ ለማዘግየት የሚቻለው በዐቃቤ ህግ ጥያቄ ወይም በፍርድ ቤቱ አነሳሽነት ሊሆን ይችላል፡፡

ንብረት እንዲወረስ ስለሚቀርብ ማመልከቻ

ፍርድ ቤቱ ንብረት እንዲወረስ ካልወሰነ በሙስና ወንጀል የተገኘ ንብረት መወረስ ጥያቄ በዐቃቤ ሕግ አመልካችነት ሊታይ ይችላል፡፡ ⓘ

ፍርድ ቤቱ ንብረት እንዲወረስ ያልወሰነ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 29 በተመለከተው መሰረት ንብረት የመውረስ ጥያቄ በዐቃቤ ህግ አመልካችነት ሊታይ ይችላል።

የንብረት መወረስ ጥያቄ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በኋላ ሊቀርብ ይችላል፡፡

ንብረቱን ለማስመለስ ለሚመለከተው አካል ስለማሳወቅ ⓘ

በሙስና ወንጀል የተገኘ ንብረት የአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የልማት ድርጅት ወይም የሌላ ግለሰብ ንብረት ወይም ገንዘብ ከሆነ ይኸው የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የልማት ድርጅት ወይም ግለሰብ በሙስና የተገኘውን ንብረት ወይም ገንዘብ እንዲመለስ በፍትሐብሄር ክስ እንዲመሰርት አግባብ ያለው አካል ሊያሳውቀው ይችላል፡፡ አግባብ ያለው አካል በመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የልማት ድርጅት የሚመሰረተውን ክስ በሚመለከት ውጤቱን ይከታተላል፡፡

ንብረትን በፍታሐ ብሔር ክስ ስለማስመለስ

በዚህ አዋጅ በአንቀፅ 29 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያየ ምክንያት ክሱ እንዲቋረጥ በመደረጉ ወይም በማንኛውም ሌላ ምክንያት የጥፋነኝነት ውሳኔ ባይስጥም በሙስና የተገኘ ንብረት እና በወንጀሉ በተገኘው ንብረት ያፈራው ንብረት ወይም በወንጀል ከተገኘው እና ከተፈራው ንብረት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ እንዲወረስ ለማድረግ ወይም በወንጀሉ ለደረሰ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን ተመጣጣኝ ዋጋን ለማስከፈል አግባብ ያለው አካል በፍትሐ ብሔር ክስ ሊመሰርት ይችላል፡፡

አግባብ ያለው አካል ተገቢ ሆኖ ሊያገኘው በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (5) ከተገለፀው ውጭ በማንኛውም ምክንያት በሙስና ወንጀል የተገኘ ንብረት እና በወንጀሉ በተገኘው ንብረት ያፈራው ንብረት ወይም በወንጀል ከተገኘው እና ከተፈራው ንብረት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ እንዲወረስ ለማድረግ፣ ወይም በወንጀሉ ለደረስ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን ተመጣጣኝ ዋጋን ለማስከፈል በፍትሐ ብሔር ክስ ሲመሰርት ይችላል፡፡

በሙስና ወንጀል የተገኘው ንብረት የመንግስት መስሪያ ቤት፣ የመንግስት የልማት ድርጅት፣ የህዝባዊ ድርጅት ወይም የሌላ ግለሰብ ንብረት ወይም ገንዘብ ሆነ ይኸው ተቋም ወይም ግለሰብ በሙስና የተገኘው ንብረት ወይም ገንዘብ እንዲመለስ በፍትሐ ብሔር ክስ እንዲመሰርት አግባብ ያለው አካል ፈቃድ ሊሰጥ ወይም ሊወክል ይችላል። አግባብ ያለው አካል እነዚህ ተቋማት የሚመሰርቱትን ክስ በሚመለክት ውጤቱን ይከታተላል።

ለፍርድ ቤት ስለሚቀርበው የማስረጃ ደረጃ

አንድ ሰው በሙስና የወንጀል ድርጊት ሳቢያ ጥቅም ያገኘ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ወይም ተመሳሽ የሚሆነውን ገንዘብ መጠን መወሰንን አስመልክቶ የሚነሱ ክርክሮችን ለማስረዳት የሚቀርበው የማስረጃ ደረጃ በፍትሐብሄር ክርክር ጊዜ እንደሚቀርበው የማስረጃ ደረጃ ይሆናል።

ተመላሽ ስለሚሆነው የንብረት ወይም የጥቅም መጠንና ንብረቱ ለመንግሥት ገቢ ስለሚሆንበት ሁኔታ ⓘ

ተከሳሹ በሙስና ወንጀል ያገኘው ንብረትና በወንጀል ከተገኘው ንብረት ያፈራው ንብረት ወይም ተመጣጣኙ ተመላሽ ይደረጋል፣

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 በተመለከተው መሠረት ተመላሽ የሚሆነው የንብረት መጠን ተከሳሹ ካገኘው ጥቅም ወይም ያገኛል ተብሎ ከሚገመተው ጥቅም ማለፍ የለበትም፣

በፍርድ እንዲወረስ ውሳኔ የተሰጠበትን ንብረት ለመንግሥት ገቢ ስለሚደረግበት ሁኔታ ዝርዝር አፈጻጸሙ በደንብ ይወሰናል፣

ተመላሽ ስለሚሆነው የንብረት ወይም የጥቅም መጠንና ንብረቱ ለመንግሥት ገቢ ስለሚሆንበት ሁኔታ

ተከሳሹ በሙስና ወንጀል ያገኘው ንብረትና በወንጀል ከተገኘው ንብረት ያፈራው ንብረት ወይም ተመጣጣኙ፣ ወይም በወንጀሉ ካደረሰው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ንብረት ተመላሽ ይደረጋል፡፡

በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) በተመለከተው ተመላሽ የሚደረገው የንብረት መጠን ተከሳሹ ካገኘው ጥቅም ወይም ያገኛል ተብሎ ከሚገመተው ጥቅም ወይም ደረሰ ተብሎ ከሚገመተው ጉዳት በላይ መሆን ወይም መብለጥ የለበትም፡፡

በፍርድ እንዲወረስ ውሳኔ የተሰጠበትን ንብረት አግባብ ያለው አካል በመረከብ ለመንግስት ያስረክባል። ንብረቱ ሙሉ በሙሉ የማይወረስ ሲሆን ወይም ከሌላ ንብረት ጋር ተዳብሎ የሚገኝ ሲሆን አግባብ ያለው አካል ንብረቱ በፍርድ አፈፃፀም መሠረት እንዲሸጥ በማድረግ ገንዘቡን ለመንግስት ገቢ ያደርጋል።

ክፍል አምስት

ቅድመ ክስ ዝግጅት

መርህ

የሙስና ወንጀል ክስ የቀረበለት ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ጭብጦችና የማስረጃው ዝርዝር ውስብስብ በመሆኑ ምክንያት የፍርድ ሂደቱን የሚያራዝመውና የሚያወሳስበው መስሎ ከታየውና በዚህ አዋጅ በአንቀጽ 36 የተመለከቱትን አላማዎች ሊያሟላ ይችላል ብሎ ካመነ የቅድመክስ ዝግጅት እንዲከናወን ሊወስን ይችላል፡፡

ቅድመ ክስ ዝግጅት ዓላማና ሂደት

የቅድመ ክስ ዝግጅት አላማ የሚከተሉት ናቸው።

ለክሱ አወሳሰን ሊረዱ የሚችሉ ጭብጦችን ለመለየት

ባለጉዳዮች ጭብጦቹን እንዲረዱ እገዛ ለማድረግ

የክሱን ሂደት ለማፋጠን

ፍርድ ቤት የክሱን አካሄድ ለመምራት እንዲያስችለው ለማገዝ

በቅድመ ክስ ዝግጅት ሂደት ፍርድ ቤቱ ⓘ

የማስረጃ ተቀባይነትን በተመለከተ በሚነሳ ጥያቄ

መደበኛው የክስ ሂደት ከመጀመሩ በፊት ውሳኔ ሊያገኝ በሚገባው በማናቸውም የህግ ጥያቄ ላይ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡

በቅድመ ክስ ሂደት ፍርድ ቤቱ፣

ዐቃቤ ሕግና ተከሳሽ በዚህ ክፍል የተጣለባቸውን ግዴታዎች መፈፀማቸውን ያረጋግጣል፤

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 130 መሠረት ለሚነሱ ጉዳዮች እልባት ይሰጣል፡፡

ዐቃቤ ሕግ የተከሳሽን መልስ ከተመለከተ በኋላ ክስ ማሻሻያ መኖር ያለመኖሩን በመጠየቅ ያረጋጣል፤ የሚሻሻል ሲኖርም ክሱን አንዲያሻሽል ዐቃቤ ህጉን ያዘዋል።

አቃቤ ህግ ግዴታ

ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህጉን፣

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 38 ሥር የተዘረዘሩትን በተመለከተ ለፍርድ ቤቱና ለተከሳሽ የጽሁፍ መግለጫ እንዲሰጥ፣

ለክሱ ሂደት ሊረዱ የሚችሉ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ እና ክሱን ለመረዳት የሚያስችል ማቴሪያል ፍርድ ቤቱ በሚያዘው ፎርም መሰረት እንዲያዘጋጅና ለፍርድ ቤትና ለተከሳሽ እንዲሰጥ፣

በእሱ አስተያየት ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል የሚላቸውን ይዘታቸው እውነትነት ያላቸውን ሰነዶች እና ሌሎች ስምምነት ሊደረስባቸው ይችላሉ የሚላቸውን ጉዳዮች ለፍርድ ቤትና ለተከሳሽ በጽሁፍ እንዲያስታውቅ፣

በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 መሰረት የቀረበውን የጽሁፍ መግለጫ የተከሳሽን ተቃውሞ መሰረት በማድረግ ፍርድ ቤቱ ተገቢ ነው ብሎ ባመነበት መንገድ አንዲያሻሽል ⓘ

በዐቃቤ ህግ የሚቀርብ የጽሁፍ መግለጫ

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 37 ንኡስ አንቀጽ 1 መሰረት የሚቀርብ የጽሁፍ መግለጫ የሚከተሉትን የያዘ መሆን ይኖርበታል፤

ለክሱ መሰረት የሆኑትን መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች፣

በአቃቤ ህግ አመልካችነት ፍርድ ቤት ሲፈቅድ የምስክሮችን ስም በምስጢር መያዝ ካላስፈለገ በስተቀር ለፍሬ ነገሩ የሚጠሩትን ምስክሮች፣

ለፍሬ ነገሩ አግባብነት ያላቸውን ኤግዚቢቶች እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎች፣

ዐቃቤ ህጉ ለክሱ መሰረት ያደረገውን የህግ ድንጋጌ፣

ከዚህ በላይ ባሉት ንዑስ አንቀጾች ከተመለከቱት የሚመነጩ ወይም የተያያዙ ናቸው ብሎ ዐቃቤ ህግ የሚያቀርባቸው፡፡

የተከሳሽ ግዴታ

ዐቃቤ ህጉ በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መሰረት ከፈጸመ በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ፣

የመከላከያውን አጠቃላይ ነጥቦች ይዘት እና በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ሊያነሳ ያሰባቸውን ጭብጦች በተመለከተ ለፍርድ ቤቱና ለዐቃቤ ሕግ የጽሁፍ መግለጫ እንዲሰጥ፣

በቀረበው ክስ ላይ ያለውን ተቃውሞ ለፍርድ ቤቱና ለዐቃቤ ህግ የጽሁፍ መግለጫ እንዲሰጥ፣

ለመከላከያው መሰረት ያደረጋቸውን የሕግ ነጥቦችና ማስረጃዎችን በተመለከተ ለፍርድ ቤቱና ለዐቃቤ ሕጉ የጽሁፍ መግለጫ እንዲሰጥ፣

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 37 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ዐቃቤ ህጉ ያቀረባቸውን ሰነዶችና ሌሎች ጉዳዮች በተመለከተ ከአቃቤ ሕግ ጋር የሚስማማባቸው ነጥቦች ካሉ እንዲገልጽ፣ ያልተስማማባቸው ካሉ ምክንያቱን እንዲገልጽ፣

ሊያዘው ይችላል።

ክፍል ስድስት

ስለ ማስረጃ

ስለትእዛዝ ይግባኝ

በዚህ አዋጅ በአንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት በሚሰጥ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ለማቅረብ ይቻላል፡፡ ሆኖም በተሰጠው ውሳኔ ምክንያት መዝገቡ ካልተዘጋ በስተቀር የጉዳዩ መታየት አይቋረጥም፡፡ ⓘ

ፍርድ ቤት መዝገቡን ስለሚዘጋበት ሁኔታ

በቅድመ ክስ ሂደት በአቃቤ ህግ የቀረበው ማስረጃ ተቀባይነት የለውም ተብሎ የተወሰነ እንደሆነ እና በዚህም ምክንያት የክስ መዝገቡ የተዘጋ እንደሆነ አቃቤ ህጉ ሌሎች ማስረጃዎችን በማሰባሰብ በተመሳሳይ ጐዳይ በድጋሚ ክስ ከማቅረብ አይከለከልም፡፡ ⓘ

ማስረጃ ስለመጠየቅ

አንድ መርማሪ ወይም አቃቤ አንድ ተጠርጣሪ በወንጀል ድርጊት ተጠቃሚ መሆኑን ወይም ከወንጀል ድርጊት የተገኘውን የጥቅም መጠን ወይም የሚገኘበትን ቦታ ለማወቅ አግባብ ያለው ሰነድ በእጁ ያለ ወይም የሚገኝበትን የሚያውቅ ማንኛውም ወይም አካል እንዲሰጠው ወይም እንዲያይ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጥያቄው አግባብነት ያለው ሆኖ ካገኘው ጉዳዩ የሚመለከተውን ሰው መጥራት ሳያስፈልግ በእጁ የሚገኘውን ወይም ይገኛል ተብሎ የሚጠረጠረውን ማስረጃ ፍርድ ቤቱ በሚወስነው ቀን ውስጥ ሰነዱን ለመርማሪው ወይም ለዐቃቤ ህጉ እንዲሰጥ ወይም እንዲያሳይ ለማዘዝ ይችላል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሶስተኛ ሰው እጅ የሚገኝ ማስረጃ ለመርማሪው ወይም ለአቃቤ ህጉ እንዲሰጥ ወይም መርማሪው ወይም አቃቤ ህጉ እንዲያየው ለማዘዝ ይችላል።

ግብረ አበርን ከክስ ነጻ ስለማድረግ

በሙስና ወንጀል ተካፋይ የሆነ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት ስለተፈጸመው ድርጊትና ስለተባባሪዎች ሚና ጠቃሚ ማስረጃ ከሰጠ በፌዴራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይም አግባብ ባለው አካል የበላይ ኃላፊ ውሳኔ ከክሱ ነፃ እንዲሆን ይደረጋል፡፡

ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም “ጠቃሚ ማስረጃ” ማለት፣

የቀረበው ማስረጃ ብቻውን በቀረበው የሙስና ወንጀል ክስ የጥፋተኛነት ውሳኔ ለማሰጠት በቂ ከሆነ፣ ወይም

ማስረጃው በመገኘቱ ሌሎች መረጃዎችንም ለማግኘት መሰረታዊ ፍንጭ ሆኖ የሚያገለግል ከሆነ፣ ወይም

የተገኘው ማስረጃ ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር በመቀናጀት የጥፋተኝነት ውሳኔ ለማሰጠት የሚያስችል ከሆነና ይኸው ማስረጃ ባለመካተቱ ወንጀሉን ለማረጋገጥ በሌላ መልኩ የተሰባሰበው ማስረጃ በቂ የማይሆን ነው ተብሎ ሲታመን፣

ነው።

ተጠርጣሪው ማስረጃውን በመስጠቱ ከክስ ነጻ የሚሆን ለመሆኑ ስልጣን ያለው ባለስልጣን በጽሁፍ ማረጋገጫ ይሰጠዋል። አግባብ ያለው አካል ከተጠርጣሪው የተገኘውን ማስረጃ በሰጠው ሰው ላይ በማስረጃነት ሊያቀርብ አይችልም።

ተጠርጣሪው በገባው ስምምነት መሰረት ማስረጃውን ካላቀረበ ወይም ተገቢውን ምስክርነት ካልሰጠ ስምምነቱን እንዳላከበረ ተቆጥሮ ያለመከሰስ መብቱ ይነሳል።

ከክስ ነጻ የተደረገ በሙስና ወንጀል ተካፋይ የሆነ ሰው የሚሰጠው የምስክርነት ቃል ክብደት ማንኛውም ምስክር ከሚሰጠው ምስክርነት እኩል ዋጋ አለው፡፡

በዚህ አንቀጽ መሠረት ከክሱ ነፃ የሚሆን በሙስና ወንጀል ተካፋይ የሆነ ሰው በወንጀሉ ያገኘው ንብረት ተመላሽ እንዲሆን ይደረጋል።

ስለአስጠቂ ምስክር

በዐቃቤ ህግ ወይም በመከላከያ ምስክርነት የቀረበ ማንኛውም ሰው በምስክርነት በተጠራበት ጉዳይ እውነቱን ለመናገር ባለመፈለግ ቀድሞ ከሰጠው የምስክርነት ቃል የሚቃረን የምስክርነት ቃል የሰጠ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ምስክሩን ያቀረበውን ወገን መሪ ጥያቄ እንዲጠይቅ ሊፈቅድለት ይችላል፡፡

ፍርድ ቤቱ መሪ ጥያቄ እንዲጠየቅ ከመፍቀዱ በፊት ተቃራኒ የምስክርነት ቃል የሰጠ መሆን አለመሆኑን ምስክሩን ይጠይቀዋል። ምስክሩ ተቃራኒ የምስክርነት ቃል መስጠቱን ከተቀበለ መሪ ጥያቄውን ይፈቅዳል።

ምስክሩ ተቃራኒ የምስክርነት ቃል መስጠቱን የካደ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ምስክሩ ተቃራኒ ቃል መስጠት አለመስጠቱን ይወስናል።

ስለኮምፕዩተር ሰነድ

በኮምፒዩተር በተገኘ ሰነድ ላይ የሰፈረ ጽሁፍ አንድን ፍሬ ነገር ለማረጋገጥ በማስረጃነት ተቀባይነት የማይኖረው፣

በኮምፒዩተር ተገቢ ያልሆነ አጠቃቀም ምክንያት በሰነዱ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ ትክክለኛ አለመሆኑን የሚያሳምኑ በቂ ምክንያቶች መኖራቸውን ወይም

ኮምፒዩተሩ ስራ ላይ ባልዋለባቸው ጊዜያት በተገቢው መንገድ የማይሰራ መሆኑን ወይም ኮምፒዩተሩ በስራ ላይ ባልዋለበት ወይም ከስራ ውጭ በሆነበት ጊዜ የሰነዱን አወጣጥ ወይም ይዘት የሚያፋልስ መሆኑን፣

ማሳየት ሲቻል ነው፡፡

ግንኙነትንና ደብዳቤን ስለመጥለፍ

ለሙስና ወንጀል ምርመራ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በስልክ፣ በቴሌኮሚኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የሚደረግ ግንኙነት እንዲሁም ደብዳቤ እንዲጠለፍ አግባብ ያለው አካል የበላይ ሀላፊ ማዘዝ ይችላል።

ለሙስና ወንጀል ምርመራ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በካሜራ፣ ድምጽ መቅረጫ እና የመሳሰሉት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች አማካይነት የተሰባሰቡ ማስረጃዎች እንደማንኛውም ማስረጃ የሙስና ወንጀል መፈጸሙን ለማስረዳት ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የሚሰጥ ትእዛዝ ለጠለፋው ምክንያት የሆነውን ወንጀል እና ጠለፋው የሚቆይበትን ጊዜ የሚጠለፈው የስልክ ግንኙነት ከሆነ ጠለፋው የሚመለከተውን የግንኙነት መስመር መግለጽ ይኖርበታል። አግባብ ያለው አካል የበላይ ሀላፊ በተለየ ሁኔታ ካልወሰነ በቀር ትእዛዙ የሚጸናው ከአራት ወር ላልበለጠ ጊዜ ይሆናል፡፡

ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ስልክ በመደወል ተገቢ ያልሆነ ጥቅም እንዲሰጠው የጠየቀ ወይም ምስክርን፣ ጠቋሚን፣ መርማሪን፣ ዐቃቤ ህግን ወይም ዳኛን ያስፈራራ ስውን ማንነት እና አድራሻ ጉዳዩ የሚመለከተው ቴሌኮሙኒኬሽን አካል እንዲያሳውቀው አግባብ ያለው አካል የበላይ ኃላፊ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ⓘ

በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀጽ (4) መሠረት የደዋዩን ማንነት እና አድራሻ እንዲያሳውቅ ጥያቄ የቀረበለት ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የሥራ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ሳይዘገይ የተሟላ መረጃ ጥያቄውን ላቀረበለት አግባብ ላለው አካል መስጠት አለበት፡፡ መረጃውን አለመስጠት ወይም መረጃውን በተሟላ መልኩ አለመስጠት አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ያስጠይቃል፡፡ ⓘ

ስለመቅዳት

ግንኙነት መቅዳትን በተመለከተ ትዕዛዙን የሚፈጽመው አካል በእያንዳንዱ ጠለፋ የተቀዳውን እና ጠለፋው የተጀመረበትንና ያበቃበትን ሰዓት መመዝገብ ይኖርበታል።

ትእዛዙ የተላለፈለት አካል በጠለፋ ከተቀዳው ውስጥ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ እውነቱን ለማወቅ የሚረዳውን በጽሁፍ አዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይኖርበታል።

ክፍል ሰባት

የሙስና ድርጊትን ስለሚጠቁሙ ሰዎች ጥበቃ

ዓላማ

የጥበቃው አላማ

የሙስና ወንጀል እንዲጋለጥ ለማበረታታት፤ እና

ጥቆማውን ያቀረበውን ሰው መብትና ጥቅም ተገቢው ግምት እንዲሰጥ ለማድረግ ነው።

ስለጥቆማ አቀራረብ

የሙስና ድርጊት የጠቋሚውን ስም ተገልጾ ወይም ሳይገለጽ አግባብ ላለው አካል ሊቀርብ ይችላል።

አንድን ጥቆማ በአግባቡ አግባብ ላለው አካል ከደረሰ ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም ጥቆማውን እንደተቀበለው ይቆጠራል።

ከሃላፊነት ነጻ ስለመሆን

በሕግ በቃለ መሀላ ወይም በስምምነት ማስረጃን በሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ያለበት ማናቸውም ሰው ማስረጃውን አግባብ ላለው አካል በመስጠቱ ህጉን ቃለ መሐላውን ወይም ስምምነቱን እንደጣሰ አያስቆጥረውም፡፡

ጥቆማውን ስለሚቀበለው አካል

አግባብ ያለው አካል ከማናቸውም ሰው የሙስና ድርጊትን በተመለከተ ጥቆማ ሲደርሰው የመቀበል ግዴታ አለበት፡፡

አግባብ ያለው አካል ጥቆማውን እንደደረሰው በመዝገብ ውስጥ ማስፈር ይኖርበታል።

አግባብ ያለው አካል የደረሰውን ጥቆማ በተመለከተ፣

ተጠሪ ለሆነው አካል ዓመታዊ ሪፖርት የማቅረብ

በስም ጥቆማ ላቀረበ ሰው በጥቆማው ላይ ስለተወሰደው እርምጃ ተገቢውን መረጃ የመስጠት ሀላፊነት አለበት፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3(ለ) መሰረት የሚሰጥ ማስረጃ ለማናቸውም ሰው ደህንነት የሚያሰጋ ወይም የወንጀሉን የምርመራ ሂደት የሚያደናቅፍ ከሆነ ማስረጃው መሰጠት የለበትም፡፡

በመዝገቡ ስለሚሰፍሩ ጉዳዮች

አግባብ ያለው አካል የሚደርሰውን ጥቆማ በተመለከተ ቢያንስ የሚከተሉትን ማስረጃዎች በመዝገብ ማስፈር ይኖርበታል።

የሚታወቅ ከሆነ የጠቋሚውን ስም

የጥቆማውን ፍሬ ሀሳብ እና

ጥቆማውን አስመልክቶ ስለተወሰደው እርምጃ

የቂም በቀል እርምጃ ህገወጥ ስለመሆኑ

ማንኛውም ሰው በሌላ በማንኛውም ሰው ላይ ጥቆማ አቅርቦአል ወይም ምስክርነት ሰጥቶአል ወይም ለማቅረብ፣ ለመስጠት አስቧል በሚል ጉዳት ማድረስ ወይም ለማድረስ መሞከር ወይም ማሴር ህገወጥ ድርጊት ነው።

አግባብ ያለው አካል ጥቆማውን እንደደረሰው በመዝገብ ውስጥ ማስፈር ይኖርበታል፡፡ ⓘ

እያንዳንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት፣ የመንግስት የልማት ድርጅት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛውን ከቂም በቀል እርምጃ ለመከላከል የሚያስችለው ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል።

በመዝገብ ስለሚሰፍሩ ጉዳዮች ⓘ

አግባብ ያለው አካል የሚደርሰውን ጥቆማ በተመለከተ ቢያንስ የሚከተሉትን ማስረጃዎች በመዝገብ ማስፈር ይኖርበታል፡፡

የሚታወቅ ከሆነ የጠቋሚውን ስም

የጥቆማውን ፍሬ ሀሳብ እና

ጥቆማውን አስመልክቶ ስለተወሰደው እርምጃ

የቂም በቀል እርምጃን ስለማገድ

የቂም በቀል እርምጃ የተወሰደበት ሰው ሰራተኛ ከሆነ በአስተዳደሩ የተወሰደበት እርምጃ እንዲታገድለት አግባብ ላለው አካል አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) አቤቱታ የቀረበለት አግባብ ያለው አካል አቤቱታውን ወዲያውኑ በመቀበል የቂም በቀል እርምጃ መኖር አለመኖሩን በማጣራት ተገቢነት ያለውን ትእዛዝ መስጠት ይኖርበታል።

በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (2) መሠረት አግባብ ያለው አካል በሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ማንኛውም ወገን እቤቱታውን በ 60 ቀናት ጊዜ ውስጥ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል። በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አቤቱታውን ለፍርድ ካላቀረበ ተቀባይነት እንዳገኘ ተቆጥሮ ውሳኔው የፀና ይሆናል።

አግባብ ያለው አካል የቁም በቀል እርምጃ በወሰደው ሰው ላይ አግባብ ባለው ሕግ መስረት የወንጀል ክስ የመሰረተ እንደሆነ በቀረበው ክስ ላይ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የእግድ ትእዛዙ እንደፀና ይቆያል።

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (4) መሠረት ለፍርድ ቤት በቀረበው አቤቱታ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በዚሁ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ እንደፀና ይቆያል።

ክፍል ስምንት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

ተፈጻሚነት ስላላቸው ህጎች

የወንጀል ሥነሥርአት ህግ፣ የፍትህብሄር ሥነሥርአት ህግ የወንጀል ህግና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ህጎች ከዚህ አዋጅ ጋር እስካልተቃረኑ ድረስ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡

ስለቅጣት

ተከሳሹ ወይም የእግድ ትእዛዙ የሚመለከተው ሌላ ሰው ፍርድ ቤት የሰጠውን የእግድ ትእዛዝ ያላከበረ እንደሆነ ተከሳሹ ወይም ትእዛዙን ያላከበረው ሰው በፍርድ ቤት መድፈር ወንጀል ከሁለት ዓመት ባልበለጠ የእስራት ቅጣት እና ከብር አስር ሺህ ባልበለጠ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

በወንጀል ህግ የበለጠ ቅጣት የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር በዚህ አዋጅ አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 1 እና አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 2 የተመለከተውን በመተላለፍ ሆን ብሎ በንብረት ላይ ጉዳት ወይም ጉድለት ያደረሰ ወይም እሽጉን የቀደደ ወይም የከፈተ ከ3 አመት በማይበልጥ እስራትና ከብር ሃያ ሺህ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

የመቀጮ ቅጣት ተፈፃሚነት ⓘ

በሙስና ወንጀል ጥፋተኝነቱ የተወሰነበትን ቅጣት ተከሳሹ መክፈል ካልቻለ በወንጀል ህግ ሥነ- ሥርዓት መሰረት ፍርድ ቤቱ የሚወስዳቸው እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው አግባብ ያለው አካል ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ፍርድ ቤቱ ያዘዋል።

ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ትእዛዝ የተሰጠው አግባብ ያለው አካል መቀጮው ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ያረጋገጣል፤ ገቢ ያልተደረገ ሲሆን ገቢ ስለሚሆንበት ወይም የማካካሻ እርምጃ ስለሚወሰድበት ሁኔታ አጥንቶ ለፍርድ ቤቱ ያቀርባል፤ ፍርድ ቤቱ በቀረበው ጥናት ላይ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

በወንጀል ያለመከሰስ መብትን ስለማንሳት ⓘ

ያለመከሰስ መብትን ስለማንሳት በሌሎች ህጎች የተደነገገው ቢኖርም የፌዴራል ወይም የክልል የሥነ- ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የበላይ ኃላፊ ለመመርመርና ለመክሰስ ስልጣን በተሰጠው ጉዳዮች ዙሪያ ያለመከሰስ መብት የማንሳት ጥያቄን እንደሁኔታው ጉዳዩን ለሚመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ወይም የክልል ምክር ቤት ሊያቀርብ ይችላል፡፡

በፈዴራልና በክልል የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች መካከል ስለሚኖር የሥራ ግንኙነት ⓘ

ሙስናን መሸከም የማይችል ህብረተሰብ በመፍጠር፣ እንዲሁም የሙስና ወንጀልን በመከላከል፣ በመመርመርና በመክሰስ ረገድ የፌዴራል እና የክልል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ተቋሞች በትብብርና በተደጋጋፊነት ይሠራሉ።

የክልል የሥነ-ምንባርና የፀረ-ሙስና ተቋሞች በኮሚሽኑ በሚሰጣቸው ውክልና መሠረት የሙስና ወንጀል ጉዳዮችን ሲመረምሩና ሲከሱ ተጠሪነታቸው ለኮሚሽኑ ይሆናል፡፡

የፌዴራል እና የክልል የሥነ-ምግባርና ሙስና ተቋሞች ለፀረ-ሙስና እንቅስቃሴው ስኬት፣ ሀገራዊ የፀረ-ሙስና ትግሉ አቅጣጫዎችን ለመንደፍና ለመተግበር፣ እንዲሁም በጋራ ለሚያከናውኗቸው ተግባራትና የሚያከናውኗቸውን አፈፃፀም ለመገምገም የሚወያዩበት የጋራ ጉባኤ ያቋቁማል ጉባኤው በተለየ ሁኔታ ካልወስነ በስተቀር የፌደራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የጋራ ጉባኤውን ይመራል።

የጋራ ጉባኤው፡-

የጋራ የአሠራር ውስጠ ደንብ ያወጣል፤

ሙስናን በመከላከል፣ በመመርመር፣ በመክሰስ እና መልካም ሥነ-ምግባርን በማስፈን ረገድ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በመገምገም የልምድ ልውውጥ ያደርጋል፤

የፀረ ሙስና ትግሉን የሚያጠናክሩ ጥናቶች የሚካሄዱበትን አቅጣጫ ይቀይሳል፣ በሚቀርቡ ጥናቶች ላይ ይወያያል፣ በጥናቶቹ መሰረት ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች እንዲወስኑ ለሚመለከተው አካል ያቀርባል ወይም እንደሁኔታውም ይወስናል፣ በሥራ ላይ መዋላቸውን ያረጋግጣል፤

ሥራውን የሚያቀናጅለት ጽህፈት ቤት ይኖረዋል። ጉባኤው በተለየ ሁኔታ ካልወሰነ በስተቀር የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የጋራ ጉባኤው ጽህፈት ቤት ሆኖ ያገለግላል፤

የጋራ ጉባኤው ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች መተገበራቸውን የጉባኤው አባላት በየበኩላቸው ይከታተላሉ።

የኮሚሽኑ አካላትና የክልል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ተቋሞች በየአካባቢያቸው ስላለው የሙስና ወንጀል ሁኔታ እና ለተከናወነ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ በሚመለከት ስታቲስቲካዊ መረጃ በየጊዜው ለጋራ ጉባኤው ጽህፈት ቤት ያስተላልፋሉ።

መሸጋገርያ ድንጋጌ

ይህ አዋጅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተፈፀሙ ወንጀሎች በነባሩ የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ልዩ የስነ ስርዓትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 434/1997 መስረት ፍፃሜ ያገኛሉ።

የተሻሩና ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ህጎች

የጸረሙስና የልዩ ሥነሥርዓትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 236/1993 እንደተሻሻለው በዚህ አዋጅ ተሽሯል፡፡

ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ ማናቸውም ሌሎች ሕጎች በዚህ አዋጅ ውስጥ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡

አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ ከጥር 25 ቀን 1997 ዓ.ም ጀምሮ የፀና ይሆናል። ጥር 25 ቀን 1997 ዓ.ም ግርማ ወልደጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት



WordPress

WELCOME TO MUHAJER SEMAN SURAFEL WEBSITES HOME ON WORDPRESS

This blog is for individuals and private organizations who want to read the FDRE Constitution as well as the interpretations of the Constitution as well as various laws of our country, various proclamations, government-approved directives, teachings and publications. Laws and the Constitution of our country. It is a website where we volunteer to help the public learn about draft laws and interpretations of the constitution

BLOG CATEGORIE'S

ABOUT CONTACT & MAPS

Share This It!