SUBSCRIBE

Search This Blog

Feb 13, 2021

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የገቢዎች ሚኒስቴር የደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 ሕገ-መንግስታዊነት ***********************************

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የገቢዎች ሚኒስቴር የደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 ሕገ-መንግስታዊነት
***********************************


ደንብ ቁጥር 155/2000 የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ሰራተኞች አስተዳደር የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ሲሆን ባሁኑ አደረጃጀት የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀፅ 36(15) መሰረት የገቢዎች ሚኒስቴር ሰራተኞች አስተዳደር ደንብ ሆኗል። በዚህ ደንብ አንቀፅ 37(1) መሰረት ዳይሬክተሩ (በአሁኑ አወቃቀር ሚኒስቴሩ) በሙስና የተጠረጠረንና እምነት ያጣበትን ማንኛዉምን ሰራተኛ መደበኛዉን ዲሲፕሊን እርምጃ አፈፃፀም ሥረዓት ሳይከተል ከስራ ማሰናብት ይችላል። በደንቡ አንቀፅ 37(2) መሰረት ደሞ ከላይ በአንቀፅ 37(1) መሰረት ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ በየትኛዉም የፍርድ አካል ዉሳኔ ወደስራ የመመለስ መብት እንደሌለዉ ተመልክቷል። 

በዚህ ደንብ አንቀፅ 37(1) ድንጋጌ መሰረት ዳይሬክተሩ (በአሁኑ አወቃቀር ሚኒስቴሩ) በሙስና የተጠረጠረንና እምነት ያጣበትን ማንኛዉንም ሰራተኛ መደበኛዉን ዲሲፕሊን እርምጃ አፈፃፀም ሥረዓት ሳይከተል ከስራ ማሰናብት ይችላል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት ዳይሬክቴሩ/ሚኒስቴሩ መደበኛዉን ሂደት ሳይከተል (summarily) ሰራተኛዉን ከስራ ለማሰናበት አንደኛ ሰራተኛዉ በሙስና መጠርጠር አለበት ሁለተኛ ዳይሬክተሩ/ሚኒስቴሩ በሙስና ከተጠረጠረዉ ሰራተኛ እምነት ማጣት ይኖርበታል። ሰራተኛዉ በሙስና ተጠርጥሯል ሊባል የሚችለዉ መቼና በምን አይነት ሁኔታ ነዉ? ጥርጣሬዉስ በቂ ጥርጣሬ ነዉ ወይስ ግምታዊ ጥርጣሬ ነዉ? የመጠርጠር ማሳያዎችና ማስረጃዎችስ በማን እይታ ይመዘናሉ? የሚሉ ጉዳዮች በትርጉምም ሆነ በዝርዝር አልተመለከቱም። ይህ መሆኑ ደሞ ከሰዉ ወደ ሰዉ የተለየ እይታ ከመፍጠሩና ወጥነት የጎደለዉ አሰራር እንዲኖር ከማድረግም አልፎ የሰራተኛዉን የስራ ዋስትና ይጎዳል። 

በደንቡ አንቀጽ 37(1) በሚሰጠዉ ዉሳኔ ወጥነት የጎደለዉ አሰራር መኖሩን ለማመላከትም በ2004 በግምገማ ዉጤት ከስራ የተሰናበቱ, በ2010 ጥቆማ ቀርቦባቸዉ የምርመራ ሂደት ተጠናቆ ከስራ የተሰናበቱ,  የዲሲፕሊን ዉሳኔ የተላለፈባቸው ፤ እንዲሁም በሰኔ 22/ 2001 የተፃፈ ደብዳቤ የገቢዉ ዘርፍ ሦስት ተቋማት በአንድ ላይ ተዋህደዉ ሐምሌ 7 ቀን በወጣዉ የኢትዮጵያ ገቢችዎና ጉመሩክ ባለስልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 587/2000 እና ይህን ተከትሎ በወጣዉ የሰራተኞች አስተዳደር ደንብ ቁጥር 155/2000 መሰረት አዲስ የሰራተኛ ምደባ ተከናዉኗል በማለት በተጠቀሰዉ ደንብ አንቀጽ 37 መሰረት ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ 
ሁለተኛዉ የድንጋጌዉ መስፈርት የዳይሬክተሩ/የሚኒስቴሩ በሙስና የተጠረጠረ ሰራተኛ ላይ እምነት ማጣት ነዉ። እምነት ማጣት ጥርጣሬን ተከትሎ የሚመጣ ጉዳይ ቢሆንም በሰራተኛዉ ላይ እምነት ማጣት በሚኒስቴሩ ግላዊ እይታ ብቻ የሚመዘን ነዉ፡፡ ይህ ደሞ ሚኒስቴሩ በህግ የተሰጣቸዉን ስልጣን መሰረት በማድረግ የዐይን ቀለሙ ያላማራቸዉን ሰራተኛ በዘፈቀደ እምነት ስላጣሁብህ ከስራ አሰናብቼሃለዉ ቢሉት የሚከለክላቸዉ አይደለም፡፡ በርግጥ ይህ ድንጋጌ ሰራተኛዉን ከሙስናና ብልሹ አሰራር ለመታደግ የተደረገ ጥረት ቢሆንም በግለሰብ እይታ ብቻ (በሚኒስቴሩ እይታ) የሚወሰነዉ ዉሳኔም ለሙስና ተጋላጭ መሆን እንደሚችል ያገናዘበ አይደለም፡፡ 

ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ደንብ አንቀጽ 37(1) መሰረት የሚሰጠዉ ዉሳኔ በማኔጅመንት መሆኑንና የሚሰጠዉም ዉሳኔ መነሻዉን የቅ/ጽ ቤት የዲሲፕሊን ኮሚቴ የዉሳኔ ሀሳብ ሆኖ የስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት የቅ/ጽ ቤቱን የዉሳኔ ሀሳብ እንደገና መርምሮ የዉሳኔ ሀሳቡን ለዳሬክተሩ (ለሚኒስቴሩ) የሚያቀርብና ሚኒስቴሩም እንዲጣራ ካደረገ በኋላ በማኔጅመንት የሚወሰን መሆኑን ከተቋሙ ያገኘነዉ መረጃ ቢያመላክትም ይህ አሰራር በህግ የተደገፈ አሰራር አይደለም፡፡ በህግ የተደገፈ አሰራር አለመሆኑ ደሞ ሀላፊ በተቀያየረ ቁጥር የተለያየ አሰራር ሊዘረጋ ከመቻሉም አልፎ በደንቡ መሰረት ያለምንም ሂደትና ምርመራ በሙስና ጠርጥሬሃለዉ ያለዉን ሰራተኛ ከስራ ለማሰናበት አያግደዉም፡፡ አሁን ባለዉ አሰራርም  ሚኒስቴሩ ከዚህ ልማዳዊ አሰራር በመዉጣት በሙስና ጠርጥሬሃለዉ ያሉትን ሰራተኛ ያለምንም ሂደት ከስራ ለማሰናበት የሚከለክላቸዉ የለም፡፡ ባጭሩ አንቀጽ 37(1) መሰረት ከ 2006 ዓ፣ም ወዲህ የሚሰጠዉ ዉሳኔ ልማዳዊ አሰራር ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ከመቅረፍ አንፃር ጥሩ ቢሆንም በህግ የተደገፈ አይደለም፡፡ በሚኒስቴሩ የህግ አማካሪና የደንቡ አርቃቂ አንቀጽ 37(1) ተፈፃሚ ለማድረግ የተካተተ ነዉ የተባለዉ የደንቡ አንቀፅ 37(2) እንደሚያመለክተዉ ደሞ ከላይ በአንቀፅ 37(1) መሰረት ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ በየትኛዉም የፍርድ አካል ዉሳኔ ወደስራ የመመለስ መብት የለዉም። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለዉ በሚኒስቴሩ/በዳይሬክተሩ የሚሰጠዉ ዉሳኔ ይግባኝ የሌለዉና የመጨረሻዉ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ማንኛዉም የፍርድ አካል ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አይኖረዉም ማለት ነዉ፡፡ 

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 37(1) መሰረት ማንኛዉም ሰዉ በፍርድ ሊወሰን የሚገባዉን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠዉ አካል የማቅረብና ዉሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለዉ፡፡ ህገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ያለዉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢሆንም የደንቡ አንቀጽ 37(2) ከህገ መንግስቱ ጋር ማየቱ ተገቢ ነዉ፡፡ አንድ ሰራተኛ ከስራ ያላግባብ ተሰናብቻለዉ የሚል አቤቱታ ለፍርድ ሰጪ አካል የሚያቀርብ ከሆነ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን የሚገባ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ በደንብ ቁጥር 155 አንቀጽ 37(1) መሰረት ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ በማንኛዉም የፍርድ አካል ወደ ስራ ሊመለስ አይችልም ማለት ደሞ በፍርድ ሊወሰን የሚገባን ጉዳይ ለማንኛዉም የፍርድ አካል አቅርቦ ወደስራ የመመለስ ዉሳኔን ሊያገኝ አይችልም ማለት ነዉ፡፡ ይህ ድንጋጌ በህገ መንግስቱ የተመለከተዉን በፍርድ አካል የመዳኘት መብትን የሚገድብ ነዉ፡፡ የዚህ ደንብ ህገ መንግስታዊነት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ በመታየት ላይ ያለ ጉዳይ ቢሆንም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ተብሎ በዚህ መልኩ የሰራተኞችን ይግባኝ የማለትና በማንኛዉም የፍርድ አካል የመዳኘት መብትን መገደቡ ተገቢ ባለመሆኑ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ሌላ የተሻለ አማራጭ መጠቀሙ ተገቢ ነዉ፡፡ 

በደንቡ አንቀጽ 37(1) የተመለከተዉ ድንጋጌ ከተቋሙ የሥራ ባህሪይ አንጻር አስፈላጊ ነዉ ቢባል እንኳን ይግባኝ የማለት መብትንና በፍርድ አካል የመዳኘትን መብት ሳይገደብ የደንቡን አንቀጽ 37(2) በማዉጣት፤ ጉዳዩን ለሚያየዉ የፍርድ አካል ሰራተኛዉ በሙስና የተጠረጠረ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ በማቅረብ ማስረዳት የተሻለ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ 
በአንቀጽ 37(1) የሚወሰነዉ ዉሳኔ ግልጽ እንዲሆንና ስልጣንን ያላግባብ በመጠቀም በአድሎ እንዳይወሰን ለማድረግ በተቋሙ ያለዉን የአሁን አሰራር በህግ መደገፍም እንደ ጥሩ አማራጭ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

WordPress

WELCOME TO MUHAJER SEMAN SURAFEL WEBSITES HOME ON WORDPRESS

This blog is for individuals and private organizations who want to read the FDRE Constitution as well as the interpretations of the Constitution as well as various laws of our country, various proclamations, government-approved directives, teachings and publications. Laws and the Constitution of our country. It is a website where we volunteer to help the public learn about draft laws and interpretations of the constitution

BLOG CATEGORIE'S

ABOUT CONTACT & MAPS

Share This It!