በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን የአስፈላጊነቱ አጥጋቢ ምክንያት ተግባራዊ ችግሮች ቢሆኑም የመንግስት አስተዳደርን ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ ረገድ ራሱን የቻለ የጐላ ጥቅም አለው፡፡ በእርግጥ የስልጣን አምባገነንነትን ሊያስከትል ከመቻሉ የተነሳ የራሱ አደጋዎችም አሉት፡፡ አደጋውና አላስፈላጊ ጐኑ ሊወገድ የሚችለው ልኩ ተለይቶ በታወቀ ገደብ ውሰጥ ተግባር ላይ የዋለ እንደሆነ ነው፡፡ ውክልናው ግልጽ፣ የማያሻማ፣ ጠባብና ገደብ የተሰመረለት ሊሆን ይገባዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ህግ የማውጣት ስልጣን ለተወካዮች ም/ቤት እንደተሰጠ በግልፅ ይደነግጋል፡፡a ይህ ስልጣን በውክልና እንዲተላለፍ የሚፈቅድ ግልጽ ድንጋጌ ግን አልሰፈረም፡፡ ስልጣኑን በውክልና እንዲያስተላልፍ የሚፈቅድለት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ባይኖርም የተለያዩ ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ ውክልና ቢያንስ በተዘዋዋሪ የተከለከለ እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል፡፡ በተለይ አግባብነት ያለው የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 77 ንዑስ አንቀጽ 13 የሚኒስትሮች ም/ቤት የተወካዮች ም/ቤት በሚሰጠው ስልጣን መሰረት ደንብ የማውጣት ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንጻር የተጠቀሰው ድንጋጌ ህግ የማውጣት ስልጣንን በውክልና ማስተላለፍ ኢ- ህገ መንግስታዊ ስላለመሆኑ በቂ መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡
ለአስተዳደር ህግ አስጨናቂው ጥያቄ ህገ መንግስቱ የተወካዮች ም/ቤት በውክልና ስልጣኑን እንዲያስተላልፍ የመፍቀዱ ነገር ሳይሆን በውክልና ሊተላለፍ የሚችለው ስልጣን ወሰንና ገደቡ የትላይ ነው? የሚለው ነው፡፡ ህግ አውጭው በህዝብ የተመረጠው ህግ ለማውጣት ነው፡፡ ስለሆነም የህግ አውጭነት ስልጣኑን ያለገደብ ወይም ሙሉ በሙሉ ለአስፈፃሚው አካል ማስተላለፍ የለበትም፡፡




















































































































































































































