SUBSCRIBE

Search This Blog

Aug 21, 2020

ጣልቃ ገብ


ጣልቃ ገብ
 



በፍትሐብሔር ክርክር ተካፋይ ያልነበረ ሰው የክርክሩ ተካፋይ የሚሆንበትና መብቱንና ጥቅሙን ለማስከበር ተገቢውን ክርክር እንዲያቀርብ በህጉ የተዘረጋ ስርዓት ጣልቃ ገብ ወደ ክርከሩ የሚገባው በተከሳሽ ጠያቂነት ወይም በራሱ አነሳሽነት ሊሆን እንደሚችል የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 41 ድንጋጌ ይዘት ያሳያል፡፡ በዚህ ድንጋጌ እንደተመለከተው ሌሎች ወገኖች በሚከራከሩበት ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሶስተኛ ወገን ከፍርድ ውሳኔ በፊት ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር እንዲፈቀድለት ሊከራከር ይችላል፡፡ ሆኖም የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብ ለመሆን ሌሎች ሰዎች በሚከራከሩበት ጉዳይ የሚሰጠው ውሳኔ በቀጥታ መብቱንና ጥቅሙን የሚነካ መሆኑን የማስረዳት ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ በሌላ አገላለፅ ጣልቃ ልግባ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲኖረው ውሳኔው የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነውን ሰው መብትና ጥቅም በሚጎዳ መልኩ በቀጥታ የሚፈጸም መሆኑንና ሌላ አዲስ ክስ በማቅረብ ለማስቀረት የማይቻል መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ጣልቃ ገብ ልሁን በሚል ጥያቄ የሚያቀርብ ሰው ውሳኔው በቀጥታ መብቱንና ጥቅሙን የማይጎዳ ከሆነ እና አዲስ ክስ በማቅረብ ማስቀረት የሚቻልበት ሁኔታ ያለው ከሆነ ጥያቄው በህግ ፊት ተቀባይነት የሚያገኝበት ሁኔታ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ጣልቃ ልግባ የሚለው ወገን በተከራካሪ ወገኖች መካከል ባለው ጉዳይ የሚሰጠው ውሳኔ መብቱን በምን አግባብና መልኩ ሊነካ እንደሚችል ማሳየት እንደአለበት የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 41(2) ድንጋጌ ያሳያል፡፡ በመሆኑም አመልካቹ ዝርዝር ምክንያቱን በማስፈር ይህንኑ የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ የጣልቃ ገብነቱ አቤቱታ ሊቀርብ የሚገባውም ጊዜ ለማራዘም፣ ክርክሩን ለማጓተት ሊሆን እንደማይገባው ከተጠቃሹ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ እንዲሁም ከፍትሃ ብሔር ስነ ስርዓት ህጉ መሰረታዊ አላማ የምንገነዘበው ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 41 በአንድ ክስ ሌሎች ተከራካሪ ወገኖች በክርክር ላይ ባሉበት ጊዜ ማናቸውም ሶስተኛ ወገን በጉዳዩ ያገባኛል የሚል ሲሆን ከፍርድ ውሳኔ በፊት ጣልቃ ገብ ሆኖ ለመከራከር እንደሚችል እና የጣልቃ ገብነት ማመልከቻው በክሱ ውስጥ ያገባኛል የሚልበትን ምክንያት የሚዘረዝርና በተለይም የመብቱን ሁኔታ የሚገልጽ መሆን እንዳለበት፣ እንዲሁም የጣልቃ ገብነት ጥያቄ አቅራቢው በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር የሚያስችል መብት ያለው መሆን አለመሆኑ በቅድሚያ ሊወሰን እንደሚገባው፣ ጣልቃ ለመግባት የሚያስችል መብት የለውም በተባለ ጊዜ መሰናበት እንደሚገባው እና መብት አለው በተባለ ጊዜ ግን የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆን ከተደረገ በኃላ ከጣልቃ ገቡ መብት አንፃር ጭምር አጠቃላይ ክርክሩ ተመርምሮ ተገቢ ነው የሚባል ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ከፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 (1)፣ (2) እና (3) ድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ቤትና ይዞታን በሚመለከት በሚደረግ ክርክር አንድ ጣልቃ ገብ አመልካች ክርክር በሚደረግበት ቤትና ይዞታ ላይ ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር መብት አለኝ በማለት መብቱን የሚያሳዩ ሰነዶችን አቅርቦ እያለ የባለይዞታነት ወይም የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር አላቀረብክም ተብሎ ከወዲሁ ጣልቃ ገብተህ ልትከራከር አትችልም ተብሎ አቤቱታውን ውድቅ ማድረግ አግባብነት የለውም፡፡


ኑዛዜ መሻር

• ተናዛዡ ቀድሞ ያደረገውን ኑዛዜ ሽሮታል ሲባል በግልፅና በማያሻማ አኳኋን ህጋዊ ውጤት ወይም ዋጋ እንዳይኖረው አድርጎታል ማለት ነው፡፡
ኑዛዜ የሟች ጥብቅ የሆነ የግል ጠባይ ያለው እና ራሱ የሚተገብረው ነው፡፡ በመሆኑም የተናዛዡ ሀሳብና ፍላጐት በጥንቃቄ ልንከተለው የሚገባው ነው፡፡ የፍ.ህ.ቁ. 898(1) ተናዛዡ ኑዛዜዎቹ ዋጋ ያላቸው እንዲሆኑ በሚያስፈልገው ፎርም ዓይነት ግልፅ አድርጎ በማስታወቅ ኑዛዜውን የሻረ እንደሆነ በጠቅላላው አኳኋን የሚሻር ይሆናል ይላል፡፡ በዚሁ ህግ አንቀፅ 899(1) ተናዛዥ የተናዘዘውን ለመሻር ወይም ለመለወጥ ያለውን ሀሳብ በቂ አድርጎ በመግለፅ ይህንን በኑዛዜው የተመለከተውን ቃል መሻር ይችላል በማለት ተደንግጔል፡፡ ሁለቱም ድንጋጌዎች አንዱ ሌላኛውን በሚያጠናክር መልኩ የተቀመጡ እንጂ የሚቃረኑ አይደለም፡፡
ይህም ሲባል ሁለቱም አንቀፆች ተናዛዡ ያደረገውን ኑዛዜ መሻር ሲፈልግ ሀሳቡን በማያሻማ አኳኋን ግልፅ በሆነ መንገድ መሻር እንደሚችል የሚገልፅ ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ሟች (ተናዛዡ) ከዚህ ውጭ ሊከተላቸው የሚገባው ሥርዓት መኖሩን አይደለም፡፡ ይልቁንም ተናዛዡ ኑዛዜውን ለመሻር ሊከተላቸው የሚገባውን አማራጮች የሚያመለክት (የሚገልፅ) ነው፡፡ ስለሆነም የኑዛዜ መሻሪያ ሰነዱ ተናዛዥና በቦታው ለነበሩ ምስክሮች የተነበበላቸው ስለመሆኑ የሚያመለክት ቃል በሰነዱ ላይ አለመስፈሩ ኑዛዜው በህጉ አግባብ እንዳልተሻረ አያስቆጥረውም፡፡
ፍ/ህ/ቁ. 881፣ 898(1)፣ 899(1)


posted from Bloggeroid

WordPress

WELCOME TO MUHAJER SEMAN SURAFEL WEBSITES HOME ON WORDPRESS

This blog is for individuals and private organizations who want to read the FDRE Constitution as well as the interpretations of the Constitution as well as various laws of our country, various proclamations, government-approved directives, teachings and publications. Laws and the Constitution of our country. It is a website where we volunteer to help the public learn about draft laws and interpretations of the constitution

BLOG CATEGORIE'S

ABOUT CONTACT & MAPS

Share This It!