የፅንሰ ሀሳቡ አፈጻጸም በአገራችን
ስለ አገራችን ፍርድ ቤቶች የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን ከመወራቱ በፊት መጀመሪያ የጽንሰ ሀሳቡ ይዘትና አፈጻጸም ምን እንደሚመስል ጥቂት መንደርደሪያ ነጥቦችን መሰንዘር ያስፈልጋል፡፡ አጣሪ ዳኝነት በአገራችን የህግና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ ያለውን ቦታ፣ አሁን የሚገኝበት ሁኔታና የወደፊት አቅጣጫዎች ጥርት ያለ ስዕል እንዲኖረን ለፅንሰ ሀሳቡ አገራዊ ፍቺ በመስጠት መጀመር ይኖርብናል፡፡ አጣሪ ዳኝነት ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ ወይም በሌላ አገር ያለው ትርጓሜ መነሻ ሀሳብ ከመፈንጠቅ በስተቀር በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ለጥያቄው ምትክ ምላሽ አይሆንም፡፡ ይህም ከሁለት ነገሮች ይመነጫል፡፡ አንደኛ፤ የአስተዳደር ህግ ከሌሎች አገራዊ ህጎች (domestic laws) በበለጠ የአንዲት አገር የህዝብ አስተዳደር፣ የፖለቲካና የህገ መንግስት ስርዓትና ታሪክ ነፀብራቅ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የአጣሪ ዳኝነት ሆነ ሌሎች የአስተዳደር ህግ መርሆዎችና ፅንሰ ሀሳቦች ከአገር አገር የጎላ ልዩነት ይታይባቸዋል፡፡ የዚህ ሀሳብ ተጓዳኝ የሆነው ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ለአጣሪ ዳኝነት የሚቀርብ ማናቸውም ትርጓሜ በፅንሰ ሀሳቡ ይዘትና አፈጻጸም ለሚነሱ መሰረታዊ ጭብጦች በከፊል ምላሹን ይሰጣል፡፡ ስለሆነም ፍቺውን ከእንግሊዝ ሆነ ከፈረንሳይ በመቅዳት በእኛ አገር በውሰት ወይም በተሞክሮ ስም ተፈጻሚ ለማድረግ ብንሞክር ‘ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’ ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የአጣሪ ዳኝነት ምንነትና አፈፃፀም በተመለከተ ከብዥታ የጠራ አመለካከት የሌለ ከመሆኑም በላይ ለፍ/ ቤት የቀረቡ በጣት የሚቆጠሩ ውሱን ጉዳዮች እንደሚያሳዩን ብዥታው በፍ/ ቤቶቻችንም ላይ በእጅጉ ይንፀባረቃል፡፡ ይህም ጽንሰ ሀሳቡ ወጥነት እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል፡፡
ከመነሻው ብንጀምር ‘ ኢትዮጵያ ውስጥ አጣሪ ዳኝነት አለ?’ የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ይነሳል፡፡ ለዚህ ወሰኑን ያልለየ ጥቅል ጥያቄ በደፈናው መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ቢሰጥም ትክክለኛ አይሆንም፡፡ የጥያቄውን ድፍንነት ገልጦ በጥልቀት ለመፈተሸ ወደ ንዑስ ጥያቄዎች መሰንጠቅና አፈጻጸሙንም በነጠላ ማጤን የሚያስማማ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያስችላል፡፡ በዚህ መልኩ ህላዌነቱም በተጨባጭ እውነታ ላይ ተመስርቶ ይወሰናል፡፡
መመለስ ያለባቸው ንዑስ ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው፡፡
-
የአገራችን ፍ/ቤቶች በአስተዳደሩ የተፈጸሙ ተግባራትን ህጋዊነት የማጣራትና የማረም የዳኝነት ስልጣን አላቸው? አላቸው ከተባለ የስልጣናቸው ህጋዊና ህገ መንግስታዊ መሰረቱ ምንድነው?
-
በአጣሪ ዳኝነት ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? በሌላ አነጋገር ፍ/ቤቶች የትኞቹን አስተዳደራዊ ተግባራት ነው ማጣራት የሚችሉት?
-
አስተዳደራዊ ውሳኔዎች (administrative acts) በፍ/ቤት ሊታዩ ወይም ሊመረመሩ የሚችሉት በየትኞቹ የምርመራ ምክንያቶች (grounds of judicial review) ነው?
-
አንድ ባለጉዳይ አቤቱታው በአጣሪ ዳኝነት እንዲታይለት ሲጠይቅ ከጥያቄ አቀራረብ ጀምሮ እስከ ‘ክስ መሰማትና’ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ ተፈፃሚ የሚሆነው ስነ-ስርዓት የትኛው ነው?
-
ፍርድ ቤቶች በአጣሪ ዳኝነት አቤቱታ ሲቀርብላቸው ምን ዓይነት ውሳኔ ማስተላለፍ ይችላሉ? ማለትም በአስተዳደራዊ እርምጃ ጉዳት የደረሰበት ወገን ከፍ/ቤቱ ምን አይነት መፍትሄ ማግኘት ይችላል?
እንግዲህ አጣሪ ዳኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ከተባለ ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ ማግኘት ይገባል፡፡ አንዳንዴ ለከፊል ጥያቄ መልስ ቢኖርም ለተቀሩት ግን ምላሽ ማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ባይሆንም ያስቸግራል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ ሂደት በመጨረሻ ሊደረስበት የሚችለው ድምዳሜ የአጣሪ ዳኝነት ጽንሰ ሀሳብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ተፈጻሚነት እንዲኖረው የዳኞች ጀብደኝነት (judicial activism) እንኳን ባይሆን ብርታት የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ በአንድ በኩል ዳኞች ለግለሰቦች መብትና ነፃነት ዘብ በመቆም በሌላ በኩል በስራ አስፈፃሚው ስራ ጣልቃ ከመግባት በመቆጠብ እነዚህን ሁለት መሰረታዊ እሴቶች በማመዛዘንና በማጣጣም ህጋዊነት የማስፈን ሚናቸውን በብቃትና በብርታት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
የአጣሪ ዳኝነት ፅንሰ ሀሳብ በአጠቃላይ ይዘቱና ወሰኑ በተለየ መልኩ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የያዘው መልክ በቀጣይ ንዑስ ምዕራፎች በጥልቀት የተዳሰሰ ቢሆንም እንደ መነሻ ያህል አንድ ቁልፍና መሰረታዊ ነጥብ ሁሌ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይኸውም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የአስተዳደር ህግ ገና ከህገ መንግስትና ከፍትሐብሔር ህግ ጉያ አልተላቀቀም፡፡ በአስተዳደሩ የሚፈጸሙ ተግባራት ህጋዊነታቸው የሚጣራው ራሱን ችሎ በቆመ የአስተዳደር ህግ ወይም የአጣሪ ዳኝነት ስርዓት አይደለም፡፡ ህግ አውጭው በህግ ነጥብ ላይ ይግባኝ ከፈቀደባቸው ውስን ጉዳዮች በስተቀር አስተዳደሩን ለተግባራቱ ተጠያቂ የሚያደርግ ከፍትሐብሔር የተለየ የአስተዳደር ፍትሕ ስርዓት ( የፍትሐብሔርና የወንጀል ፍትሕ ስርዓት እንደምንለው) የለም፡፡



















































































































































































































